Fana: At a Speed of Life!

ማዜ ብሔራዊ ፓርክን ማልማት የሚያስችል የ5 ሚሊየን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 28 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን ማዜ ብሔራዊ ፓርክን ማልማት የሚያስችለውን የ5 ሚሊየን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት ከፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ ጋር ተፈራረመ።

 

ስምምነቱን የኃይለማርያም እና ሮማን ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሮማን ተስፋዬና የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ሶኒያ ሊኦሬት ተፈራርመዋል።

 

የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የኃይለማርያም እና ሮማን ፋውንዴሽን የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ በዚሁ ወቅት፥ የድጋፍ ሥምምነቱ በቀጣይ አምስት ዓመታት ፓርኩን ለማልማት ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

 

በፓርኩ ላይ ከሚከናወኑ ስራዎች መካከልም ፓርኩን ማልማት፣ በፓርኩ ዙሪያ ያሉትን የህብረተሰብ ክፍሎች የአኗኗር ዘይቤ ማሻሻል እና ተጠቃሚ ማድረግ ተጠቃሾች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

 

አቶ ኃይለማርያም አክለውም ፋውንዴሽኑ ከማዜ ፓርክ በተጨማሪ በኦሞ እና በጋምቤላ ፓርክ ላይ የማልማት ስራ በማከናወን ላይ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

 

በደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ ፓርኮች እንዲጠበቁ እና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

 

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በብዝሃ ህይወት የበለጸገች ሀገር መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡

 

በኢትዮጵያ በርካታ ሀገር በቀል የእጽዋትና እንስሳት ዝርያዎች እንደሚገኙ በመጥቀስም፥ በማዜ ፓርክ የሚደረገው የልማት ስራም ብዝሃ ህይወትን በመጠበቅ በኩል ለሌሎች ፓርኮች አርአያ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

 

በደቡብ ክልል የሚገኘው የማዜ ብሔራዊ ፓርክ በ1997 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን 202 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት እንዳለው ተነግሯል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.