Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ ክልሎቹ የሚመሩበትን ሥርዓት ለመወሰን በቀረበ ሞሽን ላይ እየመከረ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል ምክር ቤት አዲስ በሚደራጀው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና በነባሩ የደቡብ ክልል መካከል የሚኖረውን አስተዳደራዊና ህጋዊ ጉዳዮች የሚመራበትን ሥርዓት ለመወሰን የቀረበ የውሳኔ ሀሳብ (ሞሽን) ላይ እየመከረ ነው።

 

ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች በየምክር ቤቶቻቸው በወሰኑት መሰረት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ህዝበ ውሳኔ አድርጎ የክልልነት ጥያቄያቸው መመለሱን ምክር ቤቱ አስታውሷል።

 

በመሆኑም ክልሉ ራሱን ችሎ ሲወጣ የጋራ ሀብቶችንም ለመከፋፈልና ሀብቶችን በጋራ ለመጠበቅ በመስራት በህዝቦች መካከል ያለውን አንድነት ለማጠናከር የሁሉም ሀላፊነት መሆኑን አስገንዝቧል።

 

ክልሎቹ ራሳቸውን እስከሚችሉ ድረስ የሽግግር ጊዜን በጋራ ለማሳለፍና በሁሉም ረገድ ለመደጋገፍ የጋራ ኮሚቴ ይቋቋማል ተብሏል።

 

ሞሽኑን በንባብ ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የምስረታና የነባሩን ክልል መልሶ ማደራጃ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ኑሪዬ ሱሌ፥ በክልሎቹ መካከል የሀብት ክፍፍል ተደርጎ የየራሳቸው በጀት እስከሚኖራቸው ድረስ በስምምነት የሚፈጸም የጋራ የበጀት አመዳደብ እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል።

 

ክልሎቹ ገለልተኛ አካል ባለበት የንብረት ክፍፍል እንደሚያደርጉ ጠቅሰው፥ የእዳና ሌሎችም ጉዳዮች ለዚህ ብቻ ተብሎ በሚዋቀር አብይ ኮሚቴ የሚወሰን ይሆናል ብለዋል።

 

የመንግስት ሰራተኞች በፍላጎታቸው መሰረት በሁለቱ ክልሎች በነበሩበት የስራ ዘርፍ የትምህርት ሁኔታቸው ታይቶ የሚፈፀም ይሆናልም ነው የተባለው።

 

ክልሎቹ የየራሳቸውን የፀጥታ ሀይል እስከሚኖራቸው ድረስ አሁን ያለው ሀይል አስፈላጊውን አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን የፀጥታ ሀይል አባላት በተወለዱበት አካባቢ የሚመመደቡ መሆኑን በሞሽኑ ተገልጿል።

 

ከሁለቱ ክልሎች በተጨማሪ ከዚህ ቀደም ክልል ሆነው የወጡት የሲዳማና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በጋራ የያዙት የልማት ድርጅቶች በአራቱ ክልሎች የጋራ ሀይልና የፋይናንስ አሰራር መሰረት የጋራ ክፍፍል እንደሚደረግ ተጠቅሷል።

 

ነገር ግን ክልሎቹ በጋራ እንጠቀማለን ባለበት ይቆይ የሚሉ ከሆነ በደንብ ፀድቆ እንደሚፈጸምም ነው የተገለጸው።

 

ባለትዳሮችን በተመለከተም የትዳር ህይወታቸውን በማያናጋ መልኩ ምደባ እንደሚደረግና ይህም የቤተሰብን አንድነት ለመጠበቅ ያለመ ስለመሆኑ ሞሽኑ በአንቀፅ ሶስት ላይ ደንግጓል።

 

በጥላሁን ይልማና በበረከት ተካልኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.