የሀረሪ ክልል የ2016 በጀት ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኖ ፀደቀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀረሪ ክልል ምክር ቤት ከ4 ቢሊየን 258 ሚሊየን ብር በላይ ሆኖ የቀረበለትን የክልሉን መንግስት የ2016 በጀት አፀደቀ።
ምክር ቤት ባካሄደው 6ዙር 2ኛ አመት 4ኛ መደበኛ ጉባኤ የክልሉ መንግሥት የ2016 በጀት በማፅደቅ ተጠናቋል፡፡
የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱልባሲጥ አቡበከር÷ ከተያዘው በጀት 58 በመቶ ለካፒታል በጀት እንዲሁም 42 በመቶው ደግሞ ለመደበኛ በጀት የሚውል ነው ብለዋል።
በጀቱም በዋናነት በክልሉ ከተለያዩ ገቢዎች ከሚሰበሰብ ገቢ እና ከፌዴራል መንግስት ድጎማ የሚሸፈን መሆኑን ተናግረዋል።
የፀደቀው በጀት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ25 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።
የክልሉ ምክር ቤትም በጀቱ ለታለመለት አላማ እንዲውል አቅጣጫ ማስቀመጡን ከሀረሪ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡