Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ በመጪው የግንቦት ወር ከ21 ሺህ በላይ ዜጎች የጎርፍ አደጋ ሊደርስባቸው እንደሚችል ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ በመጪው የግንቦት ወር ከ21 ሺህ በላይ ዜጎች የጎርፍ አደጋ ሊደርስባቸው እንደሚችል የብሄራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።
 
የጎርፍና የመሬት መንሸራተት ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ንቁ ሆነው መጠበቅ እንዳለባቸውም ኮሚሽኑ አሳስቧል።
 
የብሄራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ይከሰታል ተብሎ በሚታሰበው የጎርፍ አደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያና መከላከል ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።
 
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ዳመና ዳሮታ እንዳሉት፤ በሚያዚያ ወር 2012 ዓ.ም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋና የመሬት መንሸራተት ተከስቷል ነው ያሉት።
 
”በድሬደዋ ከተማ በደረሰ የጎርፍ አደጋ 4 ሰዎች ሞተዋል፤ 53 ቤቶች ሙሉ በሙሉ ፈርሰዋል፤ ሁለት ሺህ የሚጠጉ ቤተሰቦች ለምግብ እጥረት ተጋልጠዋል” ብለዋል።
በተመሳሳይ በደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልልና በሶማሌ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተ ከባድ ዝናብና ጎርፍ በመሰረተ ልማትና እንስሳት ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውሰዋል።
 
በኢትዮጵያ በአጠቃላይ በድሬደዋ፣ ሶማሌ ክልል ሸንሌ ዞን፣ ደቡብ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በደረሰ የጎርፍ አደጋና የመሬት መንሸራተት 219 ሺህ 698 ሰዎች መጎዳታቸውን ጠቅሰዋል።
 
ከ108 ሺህ በላይ ሰዎችም መፈናቀላቸውን አቶ ዳመና ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ባገኘው መረጃ መሰረት አደጋው የሚቀጥል መሆኑን ገልጿል።
 
በግንቦት ወር ብቻ ከ 21 ሺህ በላይ ሰዎች ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ስጋት መኖሩን ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
 
ከእነዚህ ጉዳት ከሚደርስባቸው ሰዎች መካከል ከ19 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
 
በመሆኑም በተለያዩ አካባቢዎች በመደበኛና ከመደበኛ በላይ በሆነ ዝናብ ቅጽበታዊ የጎርፍ አደጋ ሊደርስ እንደሚችል አብራርተዋል።
 
በተጨማሪም በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ሲዳማ፣ ሃድያ፣ ባስኬቶ፣ ጋሞ፤ በአፋር ክልል ዞን አንድና ዞን ሁለት ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
 
ምንጭ፡- ኢዜአ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.