Fana: At a Speed of Life!

ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ

ኢትዮጵያ በፈተና የምትፀና ሀገር!

ኢትዮጵያ በየዘመኑ ከውስጥና ከውጭ በሚያጋጥሟት በርካታ ፈተናዎችን አልፋ ዛሬ የደረሰች ስትሆን አንድነቷና ቀጣይነቷ በጠንካራ አለት ላይ እንዲመሠረት ካደረጉት ጉዳዮች መካከል የህዝቦቿ ህብረትና አንድነት በጉልህ የሚጠቀስ ነው፡፡ በመሆኑም የህዝቦቿ ህልውናና እጣ ፋንታም በእጅጉ የተሳሰረ ነዉ።

ኢትዮጵያን በጠንካራ መሰረት ላይ ካቆሟት እና የህዝቦቿን አንድነት ካስተሳሰሩ ዘመን ተሻጋሪ ተቋማት መካከል እንዱና ዋነኛው የሀገር መከላከያ ነው። መከላከያችን ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተወከሉበት የኢትዮጵያን ህብረብሔራዊነትን አጉልተው ከሚያሳዩት ተቋማት መካከል አንዱና ዋነኛው ሆኖ የሀገራችን የግዛት አንድነትና ሉኣላዊነት በመጠበቅ ስያገለግል ቆይቷል፤ እያገለገለም ይገኛል፡፡

ሀገር ወዳዱ፤ ቆራጡ እና ህዝባዊው መከላከያ ሰራዊታችን በሀገር ውስጥም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ በተሰጡት ግዳጆች ላይ በመሰማራት በታላቅ የሀገር ፍቅር ስሜትና በጀግንነት አኩሪ ታሪክ የገነባ ህዝባዊ ሰራዊት ነው፡፡ የሀገራችን ጋሻ እና የሰላማችን የሁል ጊዜ መከታ የሆነው መከላከያ ሠራዊታችን ኢትዮጵያን በተለያየ ጊዜ ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችንና ከውስጥ በጽንፈኛ ሃይሎች የሚቃጡባትን አደጋዎችን በማክሸፍ ኢትዮጵያን በሙሉ ክብሯ እና አንድነቷ እንድትፀና ደሙን፣ አጥንቱን እና ተኪ የሌላትን ነፍሱን ሲገብር የኖረ ሰራዊት ነው፡፡

ይህንን የሀገሪቱን ታላቅ ተቋም ጽንፈኞች ከውስጥ እና ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ከውጭ ተቀናጅተው የተለያዩ የፕሮፓጋንዳ ማሽነሪዎቻቸውን በመጠቀም ለማጠልሸትና ለማዳከም ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ቢሆንም ሰራዊታችን ህብረብሄራዊነቱን ጠብቆ ግዳጁን እየተወጣ ይገኛል፡፡በመሆኑም መከላከያን መንካት ማለት የሀገር ሉኣላዊነትን መንካት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝቦች ህልውናና እጣ ፋንታ በእጅጉ ተሳስሮ እያለ ጽንፈኛው ሃይል በአማራ ብሄራዊ ክልል የህዝብን ጥያቄ ያነገበ በማስመሰል ነፍጥ አንግቦ መከላከያ ሰራዊታችንን በማጥቃት ክልሉን የጦር አውድማ እያደረገ ይገኛል፡፡ የክልሉ ህዝብ እራሱን በራሱ የሚያስያስተዳድር ከአብራኩ በወጡ ልጆቹ የሚመራ ሆኖ ሳለ የአማራ ህዝብ ከሀገሪቱ ህዝቦች በተለየ ሁኔታ ጥያቄ ያለው በማስመሰል ነፍጥ ያነሱ እነዚህ በአቋራጭ ስልጣን ለመቆጣጠር ነውጠኛው ሃይል ክልሉን በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ወደ ኋላ እየመለሰው ይገኛል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው ጦርነት ከደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት ያላገገመውን የክልሉን ህዝብ ነጣቂው ጽንፈኛ ሃይል ዳግመኛ ለከባድ መከራ እየዳረገ ይገኛል፡፡

ከመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በደም፣ በአጥንት እንዲሁም በአስተዳደራዊ መዋቅር የተሳሰረው የአማራ ህዝብ የእርሻ ወቅትን በጠበቀ መልኩ መሬቱን በአዝርት እንዳይሸፍን መጭው ጊዜ ፈተና እንዲሆንበት ጽንፈኛው ሃይል ጋሬጣ በመሆኑ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና ህዝብን በከፍተኛ ሁኔታ ያሳስቧል፡፡
የአማራ ህዝብም ሆነ መላው የሀገራችን ህዝቦች በምርጫ የመሰረቱት መንግስት በእኩልነት ላይ የተመሰረተ የዜጎች የጋራ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ተግቶ እየሰራ ይገኛል፡፡

“እኔ ካልመራኋት” በስተቀር ሀገር አትቀናም በሚል አጉል የጽንፈኞች ነጠላ ትርክት የሚጃጃለው ጽንፈኛው ቡድን በህዝብ ጥያቄ ስም የራሱን የስልጣን ጥማት ለማርካት የክልሉን መንግስት በማፍረስ እና ክልሉን በማተራመስ የአማራን ህዝብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞችን ክፉኛ እየጎዳ ይገኛል፡፡

በዚህ ባለንበት 21ኛ ክፍለ ዘመንም ሆነ በብልጽግና መራሽ መንግስት በጠብ-መንጃ አፈሙዝ የሚመለስ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ የአማራ ህዝብ ጥያቄ ባይኖርም በህዝቡ ላይ በሚደርሰው መከራና ስቃይ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በእጅጉ ያዝናል፡፡

ስለሆነም የክልሉ ህዝብና መንግስት ከአማራ ህዝብና ከክልላዊ መንግስቱ እንዲሁም ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመሆን ይህንን ጽንፈኛ ሀይል የሚታገል መሆኑን በአጽኖት እንደሚታገለው ለመግለጽ ይወዳል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት

ነሀሴ 1/2015 ዓ.ም

ፊንፊኔ

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.