የኑሮ ጫናን የሚያቀሉ ፕሮጀክቶች ላይ በልዩ ትኩረት መስራቱ ይቀጥላል – ከንቲባ አዳነች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የነዋሪዎች የዘመናት ጥያቄ የሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እና የኑሮ ጫናን የሚያቀሉ ፕሮጀክቶች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተን መስራታችንን እንቀጥላለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡
ከተማ አስተዳደሩ “ተግዳሮቶች ያልበገረው ለውጥ” በሚል ሲያካሂድ የቆየው የ2015 በጀት ዓመት አፈፃፀም ግምገማ ተጠናቋል፡፡
ይህን አስመልክቶ ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ÷ “በ2015 በጀት ዓመት ውጤት ያገኘንባቸው ስራዎቻችን የምንረካባቸው ሳይሆኑ የጀመርናቸውን በማስፋት የነዋሪዎችን ኑሮ ለማሻሻል፣ ለኑሮ ምቹ፣ ተወዳዳሪና የኢትዮጵያ ብልፅግና ተምሳሌት የሆነች ከተማ ለመገንባት ይበልጥ ተነሳሽነት የፈጠርንባቸው ነበሩ” ብለዋል።
“የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓታችንን ቀልጣፋና ፍትሃዊ ለማድረግ የጀመርናቸው የሪፎርም ስራዎችን በማጠናከር፣ ፍትሐዊ አገልግሎት ለህዝባችን ለማድረስ፣ ሌብነትና ብልሹ አሰራርን በማስተካከልና አገልግሎት አሰጣጣችንን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ረገድ መሻሻል ቢኖርም በቀጣይ ትኩረት ሰጥተን የምንሰራው ስራ ይሆናልም” ነው ያሉት።
ለውጡ ህዝብ ፈልጎ ያመጣውና የሚደግፈው በመሆኑ ተግዳሮት የሚያደናቅፈው አለመሆኑንም ነው የገለፁት።
ይህን የህዝቡን እምነት ጉልበት በማድረግ፣ የአመራር አቅምን በማጎልበት እና ለህዝብ የሚወግኑ ተቋማትን በመገንባት የነዋሪዎች የዘመናት ጥያቄ የሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እና የኑሮ ጫናን የሚያቀሉ ፕሮጀክቶች ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
የከተማዋን ሰላም ለማስከብር ከሰላም ወዳዱ ህዝብ ጋር በመሆን ነዋሪዎች በሰላም ወጥተው በሰላም የሚገቡባት ከተማ መሆኗ ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ከንቲባዋ፥ “ለፀረ ሰላም ኃይሎች በእብሪት የሚመጣ ስልጣን እንደሌለ አሁንም ከተማችን ጥሩ ማሳያ ትሆናለች” ብለዋል።
“ጽንፈኝነትና አክራሪነት በተግባር በህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነት የተሸነፈባት፣ ሰላምዋ በዘላቂነት በህዝብ ተሳትፎ የተረጋገጠላትና ለሁሉም የምትመች፣ እንደስምዋ የተዋበች አዲስ አበባን እውን ለማድረግ በትጋት ማገልገላችንን እንቀጥላለን” ሲሉም አስፍረዋል።