አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 29፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከካናዳ አቻቸው ፍራንስዋ ፊሊፒ ሻምፓኝ ጋር በስልክ ተወያይተዋል።
ሚኒስትሮቹ በነበራቸው የስልክ ውይይት የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል ነው የተባለው።
ከዚያም ባለፈ ሁለቱ አገራት የኮሮና ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት በትብብር ለመስራት መስማማታቸው ነው የተነገረው።
በውይይቱም ወቅት አቶ ገዱ ኢትዮጵያና ካናዳ ዘመናትን ያስቆጠረ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው፤ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከር ኢትዮጵያ ትሰራለች ብለዋል።
የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን አጠቃላይ እንቅቃሴ የገለጹት ሚኒስትሩ በቀጠናውና በአፍሪካ ደረጃ የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት እየተከናወኑ ያሉ እንቅስቃሴዎችንም አብራርተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አያይዘውም ከወረርሽኙ ዓለም አቀፍ እንደመሆኑ አገራት እያደረጉት ያለውን ትብብር አጠናክረው መቀጠል እና ስርጭቱን ለመግታት ይበልጥ መረባረብ እንዳለባቸውም ነው ያነሱት።
የካናዳው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንስዋ ፊሊፒ ሻምፓኝ በበኩላቸው÷ ካናዳ ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ዋጋ ትሰጣለች ብለዋል።
ካናዳ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ከአገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑን ጠቁመው÷ወረርሽኙ በአፍሪካ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ አገራት እያደረጉት ያለውን ጥረት ካናዳ እንደምትደግፍም ገልጸዋል።
ፍራንስዋ አያይዘውም በዓለም ላይ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካናዳዊያንን ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት በሰላም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ላደረገው የማጓጓዝ አገልግሎትና አስፈላጊ ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision