Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ህዝብ ፈታኝ ጊዜያትን ሲያልፍ የመጀመሪያው አይደለም ከተባበርን ፈተናውን እንሻገረዋለን- ወ/ሮ አዳነች

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) “የኢትዮጵያ ህዝብ እንዳሁኑ ያሉ ፈታኝ ጊዜያትን ሲያልፍ የመጀመሪያው አይደለም፤ ትብብር ካለ ፈተናውን መሻገር ይቻላል” አሉ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግና የኮቪድ 19 ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ አዳነች አቤቤ።

ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በዛሬው እለት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚያስችል ክሮፕሴቭ ከተባለ የግል ድርጅት የተበረከተ የፀረ ተህዋሲሃን መርጫ መሳሪያዎችን ድጋፍን ተረክበዋል።

በዚህ ወቅትም ወይዘሮ አዳነች፥ የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መገኘቱ ከታወቀበት ጊዜ አንስቶ ይህንን ችግር ለማለፍ መንግስት የድጋፍ ጥሪ ካቀረበበበት እለት ጀምሮ ብዙ ኢትዮጵያውያን ማእድ ከማጋራት ጀምሮ በሚሊየን የሚቆጠር የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ አርያነት ያለው ተግባር መፈፀማቸውን ገልፀዋል።

በዛሬው እለት የጸረ የፀረ ተህዋሲሃን መርጫ መሳሪያ ያበረከቱትን የክሮፕሴቭ ትሬዲንግ ባለቤቶችን በራሳቸው እና በሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ስም ምስጋና አቅረበዋል።

በቀጣይም ወረርሽኙ ተለዋዋጭና ፈታኝ ከመሆኑ አንፃር ከዚህ በላይ መረዳዳት እንደሚገባና ለመከላከል የሚረዱ መሳሪያዎች እንደሚያስፈልጉ ገልጸው ከዚሁ ጎን ለጎን በህብረተሰቡ ዘንድ እየተስተዋሉ ያሉትን የግንዛቤ መዛባቶችንና መዘናጋቶችን ለማስቀረት ሁሉም በመጠንቀቅ ሌሎችንም እንዲጠነቀቁ በማሳወቅና በማስተማር በኩል በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የክሮፕሴቭ ትሬዲንግ ባለቤት አቶ አንዱአለም እንግዳ በበኩላቸው ድርጅታቸው ይህ ቫይረስ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የንፅህና መስጫ ቁሳቁሶችን ማግኘት ለማይችሉ ለተለያዩ አካላት ዕርዳታዎችን ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀዋል።

በዛሬው እለትም ዋጋቸው 350 ሺህ የሚያወጡ 160 የፀረ ተህዋሲሃን መርጫ መሳሪያዎችንና 300 ሺህ ብር በድምሩ 650 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከድርጅቱ የተበረከተውን የፀረ ተህዋሲያን መርጫ መሳሪያዎች ለኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ምርምር ኢንስቲቲት ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ አስረክበዋል።

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ምርምር ኢንስቲቲት ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ በዚሁ ወቅት፥ የፀረ ተህዋሲያን መርጫ መሳሪያ በለይቶ ማቆያ ሰፍራዎች፣ የጤና ተቋማት በአጠቃላይ ከቫይረሱ ጋር የቆዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለነበሩባቸው ሥፍራዎች እንዲሁም ለበሽታው ተጋላጭ የሚሆኑ አካባቢዎችን ፅዳት ለማድረግ መሳሪያዎቹ የላቀ አገልግሎት የሚሰጡ መሆኑን ገልፀዋል።

እንዲሁም የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለሚደረገው ርብርብ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያግዙ መሆናቸውን ጠቁመው ለተበረከተው ስጦታ ድጋፍ ላደረጉና ላስተባበሩት ምስጋናቸውን ማቅረባቸውን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.