Fana: At a Speed of Life!

የሚኒስትሮች ምክር ቤቱ የልማት ባንክ ማቋቋሚያ ደንብ ማሻሻያ ስራ ላይ እንዲውል ወሰነ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት የልማት ባንክ ማቋቋሚያ ደንብ ማሻሻያን ጨምሮ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ፖሊሲዎች ስራ ላይ እንዲውሉ ውሳኔ አሳለፈ።
 
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው እለት ባካሄደው 20ኛው አስቸኳይ ስብሰባ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን ማሳለፉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
 
ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ህጋዊ ሰውነት ለመስጠት የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ህብረቶች ያቋቋሙትን ሀገር አቀፍ ተቋም ህጋዊ ሰውነት መስጠት ተገቢ በመሆኑ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል።
 
ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ተቀብሎ ይፀድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቷል።
 
በመቀጠል ምክር ቤቱ በብሄራዊ የትራንስፖርት ፖሊሲ ላይ የተወያየ ሲሆን፥ የትራንስፖርት ዘርፉ ዝርዝር ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መስተጋብሮችን በዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ የተቀናጀ እና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል ሊመራበት የሚገባውን አቅጣጫ ማስቀመጥ የፖሊሲው ዋነኛው ትኩረት ነው።
 
የፖሊሲ ሰነዱ የትራንስፖርት ዘርፉ ተቋማዊና አስተዳደራዊ አደረጃጀቶችና ሊከተሉት የሚገባ ስትራቴጂን በመለየት ሊያሳኩት የሚፈለገውን ግብ፣ የገጠርና የከተማ ትስስር፣ ዓለም አቀፍ ትስስር እንዲሁም ከአካባቢ ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር የሀገሪቱን እድገት በማስቀጠል ረገድ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ለማድረግ የፖሊሲ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል።
 
ምክር ቤቱም በረቂቅ ፖሊሲው ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ተቀብሎ በስራ ላይ እንዲውል ውሳኔ አሳልፏል።
 
የሎጂስቲክስ ዘርፍ ፖሊሲም ሌላኛው ምክር ቤቱ የተወያየበት ጉዳይ ሲሆን፥ ፖሊሲው የሎጂስቲክስ ዘርፉን አመራር፣ አደረጃጀት እና አሰራር ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ፤ በሎጂስቲክስ መሰረተ ልማት ግንባታ እና አገልግሎት አሰጣጥ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ እንዲሁም የሎጂስቲክስ ዘርፍ ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ከሌሎች የኢኮኖሚ መስኮች ጋር ተደጋጋፊ ሆኖ እንዲያድግ ለማስቻል ብሄራዊ የሎጂስቲክስ ዘርፍ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል።
 
የሚኒስትሮች ምክር ቤትም በረቂቅ ፖሊሲው ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ተቀብሎ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል።
 
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ማቋቋሚያ ደንብ ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይም ምክር ቤቱ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
 
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የፖሊሲ ባንክ በመሆኑና የሀገሪቱን የልማት እቅድ ለማስፈፀም አቅም እንዲኖረው የባንኩን ካፒታል ማሳደግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ካፒታሉን ለማሻሻል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ነው ለምክር ቤቱ የቀረበው።
 
የሚኒስትሮች ምክር ቤትም የማሻሻያ ረቂቅ ደንቡን በማፅደቅ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እንዲወጣና በስራ ላይ እንዲውል ውሳኔ አሳልፏል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.