Fana: At a Speed of Life!

የሽብር ስጋቶችና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል የቀጠናው ሀገራት በትብብር መስራት እንደሚገባቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ ቀንድ የሽብር ስጋቶችና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀጠናው ሀገራት በትብብር መስራት እንደሚገባቸው ተገለጸ

ኢትዮጵያን፣ ኬኒያ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲና ሲሼልስን ያካተተ እና የአገራቱ የመረጃና ደኅንነት ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የተሳተፉበት የምክክር ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳሬክተር ጀኔራል አቶ ታዜር ገ/እግዚአብሄር የምክክር መድረኩን በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ምስራቅ አፍሪካ ለሽብርተኞች ምቹ የሆነ ቀጠና ብቻ ሳይሆን ሽብርተኝነት አሁንም የቀጠናው የፀጥታ ስጋት ችግር ሆኖ ቀጥሏል፡፡

በተለይ የአልሸባብ እና የአይ ኤስ የሽብር ቡድኖች በቀጠናው የተለያዩ አገራት ውስጥ መረባቸውን ዘርግተው እኩይ ተግባራቸውን ለመፈጸም ሌት ተቀን እየጣሩ ነው ።

እነዚሁ ሽብርተኛ ቡድኖች በፋይናንስ፣ በሰው ኃይል ምልመላ፣ በስልጠናና ቁሳቁስ በመደጋገፍ የጥፋት ሴራቸው ሥር እንዲሰድ ያላሳለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

ቀጠናው ለህገወጥ የሰዎች ዝውውር መተላለፊያ፤ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ንግድ እና ድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎች በስፋት የሚስተዋልበት መሆኑ ለዚህ እኩይ ድርጊታቸው ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል ብለዋል።

ከሽብርተኞች ጋር የሚደረግ ትግል በአንድ አገር ጥረት ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ የፀረ-ሽብር ዘመቻን ሀገራቱ በትብብርና አጋርነት በጋራ ሊያከናውኑ እደሚገባ አቶ ታዜር አብራርተዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ሽብርተኝነትን በመከላከል ረገድ ከውጭ አቻ የመረጃና ደኅንነት ተቋማት ጋር በተከናወኑ የትብብር ስራዎች ሊፈጸሙ የነበሩ የሽብር አደጋዎችን በመቀልበስ በሴራው እጃቸው ያለበትን 165 የአልሸባብ አባላት እንዲሁም 121 የአይ ኤስ አባላት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረጉ አስታውሰዋል፡፡

በምስራቅ አፍሪካ በተለይም በህንድ ውቅያኖስ አዋሳኝ ሀገሮች ውስጥ በአሸባሪ ቡድኖች እና ድንብር ተሻጋሪ የተደራጁ የወንጀል ኔትወርኮች መካከል ያለው ትስስር እየጨመረ መምጣቱ በመድረኩ ተገልጿል።

የሽብር ስጋቱን ለመግታት በሁለትዮሽ፣ በክፍለ አህጉር፣ በአህጉር እና በአለም አቀፍ ደረጃ ይበልጥ የተቋማት ትብብርን እና ቅንጅትን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑ ተጠቁሟል።

የሽብር ቡድኖችን ምልመላ፣ ፕሮፓጋንዳን እና ጽንፈኝነትን መከላከል ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎችን ማጠናከር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተገልጿል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መረጃ እንዳመለከተው፤ የሽብር ቡድኖችን እና የወንጀል ኔትወርኮችን በጋራ የድንበር ስራዎች ለመከላከል የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ትብብርን ማጠናከር አስፈላጊነት ላይ ከስምምነት ተደርሷል።

በዚሁ መሰረትም የሽብርተኞች የፋይናንስ ምንጭን መለየትና ማድረቅ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ጨምሮ የጸረ-ሽብር ዘመቻን በጋራ በማካሄድ ውጤታማ ሊያደርጉ የሚያስችሉ 20 ነጥቦችን የያዘ ምክረ ሃሳብን በማስቀመጥ የምክክር መድረኩ ተጠናቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.