Fana: At a Speed of Life!

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ተማሪዎች እውቀትን መገብየት አላማቸው አድርገው እንዲጓዙ አሳሰቡ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቅርቡ ወደ ተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የሚሄዱ ተማሪዎች በጉዟቸው ከዲግሪ ባሻገር እውቀትን መገብየት አላማቸው አድርገው እንዲጓዙ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) አሳሰቡ፡፡

ሚኒስትሩ÷ በቅርቡ ወደ ተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ለሚሄዱ የነጻ ትምህርት እድል ተጠቃሚዎች ልምዳቸውን አካፍለዋል።

በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የመሰብሠቢያ አዳራሽ ለተማሪዎቹ ባደረጉት ገለጻ÷ በጉዞና የትምህርት ቆይታቸው ሊያግጥሙ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ምክርና ልምዳቸውን አካፍለዋል።

ተማሪዎች በጉዟቸው ከዲግሪ ባሻገር እውቀትን መገብየት አላማቸው አድርገው እንዲጓዙም ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡

ተማሪዎቹ በብሄራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት እንዳስመዘገቡት በተመሣሣይ በውጭ አገርም በጥሩ ስነ ምግባር በርትተው በማጥናት አገራቸውን ማስጠራት እንደሚጠበቅባቸው መክረዋል።

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጁ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ተማሪዎቹ በርትተው በመማር ተመልሰው አገራቸውን ያገለግላሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የስኮላርሺፕና ዓለም አቀፋዊነት ዴስክ ሀላፊ ኢዶሳ ተርፋሳ (ዶ/ር)÷ ተማሪዎቹ አስፈላጊውን የጉዞና የትምህርት ማስረጃ ሠነድ በማሟላት የጉዞ ዝግጅት እንዲያደርጉ ማሳሰባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥያቄ መሠረት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መንግስት በ12ኛ ክፍል ፈተና የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ 273 ተማሪዎች ሙሉ ነጻ የትምህርት እድል መስጠቱ ይታወቃል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.