የአማዞን አካባቢ ሀገራት የደን ጭፍጨፋን ለማስቆም በጠሩት ስብሰባ መስማማት አልቻሉም
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ስምንት የደቡብ አሜሪካ ሀገራት በብራዚል ባካሄዱት ስብሰባ ለአደጋ ተጋላጭ የሆነውን አማዞን ደንን ከጭፍጨፋ ለመታደግ በጋራ ግብ ላይ መስማማት እንዳልቻሉ ተገልጿል።
የአማዞን የትብብር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኤ ሲ ቲ ኦ) አባል ሀገራት ከአስር ዓመት በኋላ ነው ‘የዓለም ሳንባ’ በመባል የሚታወቀውን ደን ለመታደግ ቁርጥ ያለ ግብ ማውጣትን ዓላማ ያደረገ ስብሰባ ለመጀመሪያ ጊዜ ያካሄዱት፡፡
በ14 ዓመታት ውስጥ እንዳልተገናኙ የገለፁት የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ አሁን ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች እና ከፊት የተደቀኑ ዕድሎች የጋራ እርምጃ በመፈለጋቸው ለመገናኘት እንዳስገደዳቸው አንስተዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በፈረንጆቹ 2030 የደን ጭፍጨፋን ለማስቆም የጋራ ቀጣናዊ ፖሊሲ እንዲቀረፅ በማበረታታት በሀገራቸው የደን ጭፍጨፋን ዜሮ ለማድረስ እንደሚሰሩም ቃል ገብተዋል።
በቀድሞ የሀገሪቱ መሪ ጃዬር ቦልሶናሮ አስተዳደር ዘመን የብራዚሉ አማዞን ደን ጭፍጨፋ በከፍተኛ ሁኔታ እንደጨመረ የጠቆሙት አንዳንድ ተመራማሪዎች፥ ጥቅጥቁ ደን ወደ ዛፍ አልባ የሳር ሜዳነት ሊቀየር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
የብራዚል፣ የኮሎምቢያ፣ ፔሩ እና ቦሊቪያ መሪዎች ከኢኳዶር፣ ቬንዝዌላ፣ ጉያና እና የሱሪናም ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር አማዞንን በጋራ ለመታደግ የሚያስችል ‘የቤሌም አዋጅ’ የተሰኘ የአካባቢ ጥበቃ ሰነድ መፈራረማቸውን ሲ ኤን ኤን ዘግቧል።
ይሁንና በዋናው እና የደኑን ጭፍጨፋ ማስቆም በሚቻልበት የጋራ ፖሊሲ ላይ አለመስማማት መፈጠሩ ነው የተዘገበው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ጉያና፣ ሱሪናም እና ቦሊቪያ በጋራ ግብ ላይ ባለመስማማት ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸውም ተነግሯል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!