የሻምቡ ባኮ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው የሻምቡ ባኮ የአስፋልት ኮንክሪት የመንገድ ግንባታ ስራ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።
መንገዱ 60 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን 993 ሚሊየን 280 ሺህ 400 ብር ወጪ ተደርጎበታል።
መንገዱ በወረዳ ከተማ የመንገድ ትከሻን ጨምሮ 19 ሜትር ፣ በገጠር ደግሞ 10 ሜትር ስፋት አለው፡፡
ግንባታውን የቻይናው ሲ ጂ ሲ ኦቨርሲስ ዓለም አቀፍ የስራ ተቋራጭ ድርጅት አከናውኖታል።
የግንባታ ወጪው ከዓረብ ባንክ፣ ከኦፌድና ከኢትዮጵያ መንግስት በተገኘ ገንዘብ የተሸፈነ ሲሆን፥ መንገዱ የሆሮ ጉድሩ ወለጋን እና የምዕራብ ሸዋ ዞኖችን ለማገናኘት ያስችላል ተብሏል።
እንዲሁም በአካባቢው ለሚገኙ ነዋሪዎች፣ አጎራባች ዞኖች እና ወረዳዎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል ተብሎ ይታመናል ነው የተባለው።
ከዚህ በተጨማሪም ከፊንጫ ስኳር ፋብሪካ የሚመረቱ የምርት ውጤቶችን በአቋራጭ ወደ ገበያ ማዕከላት እንዲቀርቡ ከማስቻል አንፃር የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።