በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ በአፍሪካ እስከ 190 ሺህ ሰዎች በመጀመሪያው ዓመት ህይዎታቸው ሊያልፍ ይችላል – የዓለም ጤና ድርጅት
አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 30 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ ከ83 ሺህ እስከ 190 ሺህ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ በመጀመሪያው ዓመት ብቻ ህይዎታቸው ሊያልፍ እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት አስጠነቀቀ።
ድርጅቱ ትናንት ባወጣው መግለጫ በአፍሪካ ሃገራት ቫይረሱን ለመከላከል የወጡ መመሪያና ህጎች ተግባራዊ እየተደረጉ አለመሆኑን እና እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችም በቂ አለመሆናቸውን አስታውቋል።
ቫይረሱ ወደ አህጉሪቱ ዘግይቶ ቢገባም ለበርካታ ጊዜ የሚቆይ ወረርሽኝ ሊሆን ይችላልም ነው ያለው።
በተጨማሪም ቫይረሱን በፍጥነት በቁጥጥር ስር ማዋል ካልተቻለ ከ29 እስከ 44 ሚሊየን ሰዎችን ሊይዝ እንደሚችልም ነው ያስጠነቀቀው።
የአሁኑ የድርጅቱ መረጃ በ47 የአፍሪካ ሀገራት የሰራውን ጥናት መሰረት አድርጎ የወጣ ነው ተብሏል።
ከሃገራቱ መካከል ደቡብ አፍሪካ፣ አልጄሪያ እና ካሜሩን በቫይረሱ ክፉኛ ሊጠቁ የሚችሉ ሃገራት ይሆናሉ በሚልም ስጋቱን አስቀምጧል።
በጥናቱ ግብጽ፣ ሊቢያ፣ ቱኒዚያ፣ ሞሮኮ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ጂቡቲ አልተካተቱም።
በአፍሪካ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ በ47 ሃገራት ከ35 ሺህ በላይ ሰዎች ሲያዙ፥ ከ1 ሺህ 200 በላይ ደግሞ ሕይወታቸው ማለፉን ድርጅቱ ገልጿል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።