Fana: At a Speed of Life!

በሐሰተኛ ደረሰኝ ከ30 ቢሊየን ብር በላይ በመሸጥ በከፍተኛ የማጭበረበር ወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ዋለ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሐሰተኛ የሽያጭ ደረሰኝ አዘጋጅቶ ለተለያዩ ነጋዴዎችና ድርጅቶች ከ30 ቢሊየን ብር በላይ በመሸጥ በከፍተኛ የማጭበረበር ወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ በአዲስ አበባ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።

ተጠርጣሪው አድራሻው የማይታወቅ ሰለሞን ሙሉ ከውን በተባለ ግለሰብ ሐሰተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት በዚሁ መታወቂያ የተዘጋጀ የንግድ ፍቃድ በማውጣት የማሽነሪዎች እና የመሣሪያዎች ኪራይና ሽያጭ የንግድ ዘርፍ ላይ ተመዝግቦ እንደነበር ተመላክቷል፡፡

በዚኅም ምንም ዓይነት የንግድ ልውውጥ ሳያደርግ የሸጠው እቃ ሳይኖር ሐሰተኛ የሽያጭ ደረሰኝ ለተለያዩ ነጋዴዎችና ድርጅቶች በ30 ቢሊየን 152 ሚሊየን 434 ሺህ 2 ብር ከ03 ሣንቲም በመሸጥ መጠርጠሩ ተጠቁሟል፡፡

ግለሰቡ የማጭበርበር ወንጀሉን ከፈፀመ በኋላ ለበርካታ ጊዜያት ተደብቆ የነበረ ቢሆንም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ጋር በመተባበር ባደረገው ጠንካራ ክትትል በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በተጠርጣሪው ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጾ ፥ኅብረተሰቡም ወደ ኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ቢሮ በአካል ቀርቦ ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.