አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከኢስቶኒያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በስልክ ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 30 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋችው ከኢስቶኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኡርማስ ሬይንሳሉ ጋር ተወያዩ።
በውይይታቸውም የሃገራቱን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች እና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በትብብር መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በስልክ መክረዋል።
አቶ ገዱ ኢስቶኒያ የወቅቱ የጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በመሆን በመመረጧ የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ፥ የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው የተሳካ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከኢስቶኒያ ጋር የምታደርገውን የሁለትዮሽ እና የዓለም አቀፍ መድረክ ትብብር ይበልጥ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አቶ ገዱ በውይይታቸው አንስተዋል።
የኮሮና ወረርሽኝ የሰውን ህይወት በእጅጉ እየቀጠፈ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ገዱ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እና የባሰ ጉዳት እንዳያደርስ የሁሉም አካላት ትብብር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በቀጠናው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እየተጫወተች ያለውን ሚና ያብራሩት አቶ ገዱ፥ የቀጠናውን ኢኮኖሚ ትርጉም ባለው መልኩ የሚቀይረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ በተመለከተም ገለጻ አድርገዋል።
የኢስቶኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኡርማስ ሬይንሳሉ በበኩላቸው ለመልካም ምኞት መግለጫው አመስግነው፥ ኢስቶኒያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ትሰራለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የምታደርገውን የጎላ ሚና እንደሚያደንቁም አውስተዋል።
ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብጽ መካከል የሚነሱ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ በሚደረግ ውይይት ብቻ መፈታት እንዳለባቸውም አስረድተዋል።
ይህ እንዲሳካ ሃገራቸው የበኩሏን አስተዋጽኦ ታደርጋለች ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።