በተፈጥሮ በሴቶች ላይ የሚስተዋልን የስትሮክ ተጋላጭነት ለመቀነስ ምን መደረግ አለበት?
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ስትሮክ ወደ አንጎል አካባቢ ያለው የደም ፍሰት ሲዘጋ ወይም በአንጎል ውስጥ ያለው የደም ቧንቧ ሲበጠስ በወንዶችም ሆነ በሴቶች ላይ የሚከሰት ህመም ነው፡፡
ከላይ ከተገለጹት የህመሙ መከሰቻ ምክንያቶች በተጨማሪ ሴቶች በተፈጥሮ ምክንያት ለስትሮክ የሚጋለጡባቸው ሁኔታዎች መኖራቸውን ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
ለአብነትም፥ አንዳንድ የሆርሞን ዓይነቶችን መጠቀም፣ ወሊድ፣ እርግዝና፣ የወሊድ መከላከያ ክኒኖች እና የማይግሬን ራስ ምታት የሚሉትን ያነሳሉ፡፡
በግልጽ ከሚታወቁት የስትሮክ ምልክቶች (የፊት መውደቅ፣ የክንድ ድክመት፣ የንግግር ችግር፣ የአንድ ወይም የሁለቱም ዓይኖች የማየት ችግር፣ ሚዛንን አለመጠበቅ እና ከባድ ራስ ምታት) በተለየ÷ በአንዳንድ ሴቶች ላይ እንደ ድካም፣ ማቅለሽለሽ፣ የሰውነት መዛል፣ ማስታወክ ወይም የማስታወስ ችግር ያሉ ስውር የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ሊስተዋሉ እንደሚችሉም ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
ማጨስ፣ የደም ግፊትና የኮሌስትሮል መጠን መጨመር በሴቶችና ወንዶች ላይ የስትሮክ መንስኤ ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡
ሴቶች በተፈጥሮ ምክንያት ለስትሮክ የሚጋለጡበትን ሁኔታ ለመቀነስ ከታች የተዘረዘሩትን ጉዳዮች በሕክምና ባለሙያ ድጋፍ ማከናወን እንደሚገባ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ መረጃ ያመላክታል፡፡
1. ከእርግዝና ጋር የተያያዘ የደም ግፊት ያለባቸው ሴቶች ለስትሮክ የመጋለጥ ዕድላቸው 2 እጥፍ፤ ለደም ግፊት የመጋለጥ ዕድላቸው 4 እጥፍ ስለሆነ÷ ከእርግዝና በፊት ከፍተኛ የደም ግፊት ታሪክ ያላቸው ሴቶች ዝቅተኛ መጠን ያለው የካልሲየም ማሟያ በመውሰድ ከእርግዝና ጋር የተያያዘ የደም ግፊት ስጋትን እንዲቀንሱ፤
2. መካከለኛ የደም ግፊት (150 -159 / 100 – 109) ያለባቸው እርጉዝ ሴቶች የደም ግፊት መድሃኒት እንዲወስዱ፤ ለመውለድ የተቃረቡ ከፍተኛ የደም ግፊት (ከ160/110 በላይ) ያለባቸውም የህክምና ክትትል እንዲያደርጉ፤
3. የስትሮክ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የወሊድ መከላከያ እንክብሎችን ከመውሰድ በፊት የደም ግፊትን መመርመር፤
4. የማይግሬን ራስ ምታት ያለባቸው ሴቶች ከፍተኛ የሆነ የስትሮክ ስጋትን ለማስወገድ ሲጋራ ማጨስ እንዲያቆሙ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡