በክልሉ የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል 1 ነጥብ 2 ሚሊየን አጎበር ተሰራጨ
በክልሉ የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል 1 ነጥብ 2 ሚሊየን አጎበር ተሰራጨ
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 14 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በ2015 በጀት ዓመት 1 ሚሊየን 236 ሺህ የጸረ ወባ አጎበር ለህብረተሰቡ መሰራጨቱን የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት አስታወቀ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምራት ቦጋለ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት÷ የወባ በሽታ ወረርሽኝ በክልሉ ሁሉም ዞኖች በ42 ወረዳዎች በመኖሩ ጫና እያሳደረ ይገኛል።
ቤንች ሸኮ፣ ምዕራብ ኦሞ እና ዳውሮ ዞኖች ደግሞ ከሌሎች ዞኖች አንፃር ከፍተኛ የህሙማን ቁጠር የተመዘገባቸው እንደሆኑ ቁመዋል፡፡
በክልሉ በአጠቃላይ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ሰዎች የወባ በሽታ ተጋላጭ መሆናቸውን እና 420 ሺህ ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የወባ በሽታ ወረርሽኝ መሆኑ ታውቆ የተለያዩ የመከላከል ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ለአብነትም በህዝብ ተሳትፎ የሚሰሩ ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ጨምሮ አጎበርን ለህብረተሰቡ የማዳረስና የኬሚካል ርጭት መካሄዱን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ባለፈው በጀት ዓመት በተለይም ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ አካባቢዎች ቅድሚያ በመስጠትበ በ30 ወረዳዎች የኬሚካል ርጭት መደረጉን እና በ42 ወረዳዎች 1 ሚሊየን 236 ሺህ አጎበር መሰራጨቱን እና ሽፋኑም 93 በመቶ መዳረሱን ጠቁመዋል፡፡
በኬሚካል ርጭት በኩልም በ2015 በጀት ዓመት በ128 ሺህ ቤቶች ርጭቱ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡
የወባ በሽታ መድሃኒትም በሁሉም ደረጃ እንዲደርስ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀው፤ ወቅቱም ለወባ ትንኝ ርቢ ተስማሚ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታትም የበሽታ ስርጭቱ የመቀነስ አዝማሚያ እያሳየ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የወባ በሽታ በመከላከል ስራ ውስጥ የኬሚካል እጥረት እና የህብረተሰቡ የአጎበር አጠቃቀም ችግር እንዳለ ተናግረው ይህን መቅረፍ ከተቻለ በሽታውን መቆጣጠር የሚቻልበት ሁኔታ እንዳለ ተናግረዋል።
በፌቨን ቢሻው