የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ድጋፍ ለሚሰጡ የጤና እና ሌሎች ባለሙያዎች የህይወት መድን ሽፋን ሊሰጥ ነው
አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 30 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ድጋፍ ለሚሰጡ የጤና እና ሌሎች ባለሙያዎች የህይወት መድን ሽፋን ለመስጠት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ።
ስምምነቱን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እና የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነጻነት ለሜሳ ፈርመዋል፡፡
በስምምነቱ መሰረትም የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በተለያዩ የጤና ተቋማት ለሚሰሩ የጤና እና ለሌሎች ባለሙያዎች የህይወትና የአደጋ መድን ሽፋን ይደረግላቸዋል።
ይህም በለይቶ ማቆያ፣ በኳራንቲን፣ በላብራቶሪ ምርመራ ማዕከል፣ በፈጥኖ ምላሽ ቡድን፣ በድንገተኛና በሌሎች ክፍል የሚሰሩ ባለሙያዎችን ይሸፍናል ተብሏል።
ጎን ለጎንም ጽዳቶች፣ የአንቡላስ ሹፌሮችና ሌሎችም ፊት ለፊት የሚሰሩ ባለሙያዎች በዚሁ የህይወት መድን ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።