በደቡብ ክልል አሌ ልዩ ወረዳ በደረሰ የመሬት ናዳ የ12 ሰዎች ህይወት አለፈ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 1፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል አሌ ልዩ ወረዳ ጎሮዜ ቀበሌ ትናንት በተከሰተ የመሬት ናዳ የ12 ሰዎች ህይወት አለፈ።
ህይወታቸው ካለፈ ሰዎች መካከልም እስካሁን የ5 ሰዎች አስከሬን መገኘቱ ነው የተገለፀው።
የመሬት ናዳው በስድስት የመኖሪያ ቤቶች ከእነ ሙሉ ቤተሰቦቻቸው ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆም፥ የቀሪ ሟቾችን አስከሬን የማፈላለግ ስራው ቀጥሏል።
ናዳው ከፍተኛ እንደመሆኑ መጠን ከሰው ጉልበት በተጨማሪ ማሽነሪ በመጠቀም አስከሬን ለማፈላለግ ጥረት ቢደረግም አካባቢው ረግረጋማ በመሆኑ የነብስ አድን ስራውን ፈታኝ እንዳደረገውም ተመልክቷል።
በአሁኑ ወቅት በመሬት ናዳው ለተፈናቀሉ ዜጎች መጠለያ ሸራ የማቅረብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የወረዳው አስተዳደር አስታውቋል።
የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው በደረሰው አደጋ ህይወት በመጥፋቱ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በራሳቸውና በክልሉ ህዝብ ስም የገለጹ ሲሆን፥ ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም የክልሉ መንግስት በዘርፉ የሚደረገውን ተግባር እንደሚደግፍ ማስታወቃቸውን ከደቡብ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።