አሜሪካ ኢትዮጵያ የኮቪድ19 ስርጭትን ለመግታት የምታደርገውን ጥረት ለማገዝ ከ37 ሚሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ አድርጋለች
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 1 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ኢትዮጵያ የኮቪድ19 ስርጭትን ለመግታት የምታደርገውን ጥረት ለማገዝ እስካሁን ከ37 ሚሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ አድርጋለች።
ድጋፉ በዋናነት ኮቪድ19ኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችልና የማህበረሰቡን ተጋላጭነት ለመቀነስ እንዲሁም ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ከአሜሪካ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የሃገሪቱ መንግስት ከኢፌዴሪ የጤና ሚኒስቴር፣ የሰላም ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የአደጋ ስጋት እና ስራ አመራር ኮሚሽን እና ሌሎች ዓለም አቀፍና ሃገር በቀል አጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለውን ጥረት እያገዘ መሆኑንም አስታውቋል።
ድጋፉ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ፣ የተጋላጭነት መጠነን ለመቀነስ እና ለመቆጣጠር፣ የኮቪድ19 ምርመራ የሚያደርጉ ላቦራቶሪዎችን አቅም ለማሳደግ፣ ማህበረሰቡ የቫይረሱን ስርጭት መከላከልና መቆጣጠር የሚችልበትን አግባብ ለመፍጠር የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን ለመስጠት የሚያስችል ነው ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ከተለያዩ ሃገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች የሚደረገውን የልየታና ምርመራ ስራ ለማጠናከር ያግዛልም ነው የተባለው።
የአሜሪካ መንግስት ባለፉት 20 አመታት ውስጥ በጤናው ዘርፍ የ4 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፥ በተለያዩ የልማት ዘርፎች ድጋፍ አድርጓል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ “ኢትዮጵያ የኮቪድ-19ን አስከፊ ተጽዕኖ ለመከላከል በምትጥርበት በዚህ ወቅት፣ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ስለሚያደርገው ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ላመሰግን እወዳለሁ” ሲሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ይሄንን ፈተና ሁላችንም በአሸናፊነት የምናልፈው፣ በአጋርነት እና በጋራ አመራር ነውም ብለዋል።