Fana: At a Speed of Life!

ቻይና ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 16/2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በተለያዩ ዘርፎች ያላትን ትብብር አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች፡፡

በአፍሪካ ህብረት የቻይና ሚሲዮን ኃላፊ አምባሳደር ሁ ቻንግቹን ስለሀገራቸው ወቅታዊ ምጣኔ ሀብት፣ የቻይና-አፍሪካ ትብብር እና ተያያዥ ጉዳዮች በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

አምባሳደሩ በመግለጫቸውም ÷ቻይና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል እና ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ለአፍሪካ ሀገራት የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።

አምባሳደር ሁ ቻንግቹን ስለሀገራቸው ወቅታዊ ምጣኔ ሃብት እድገት፣ የቻይና-አፍሪካ ትብብር፣ የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ የ10 ዓመታት ጉዞ፣ የታይዋን ጉዳይ፣ የወቅቱን የብሪክስ ጉባኤ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖና መሰል ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ቻይና በኢንዱስትሪ ልማት፣ የድህነት ቅነሳ እና የምጣኔ ሃብት ማገገሚያ ድጋፎችን ለአፍሪካ ሀገራት ስታደርግ መቆየቷንም አምባሳደሩ አንስተዋል፡፡

የአፍሪካ ሀገራት የአጀንዳ 2063 ግቦቸ ለማሳካት የሚያደርጉትን ጥረት፣ በአህጉሪቱ የሚከናወኑ የልማት፣ ሰላም እና ፀጥታ ተግባራትን ለመደገፍ ቻይና ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል።

ለዚህም በአህጉሪቱ የኢንዱስትሪ አቅም ልማት ላይ ቻይና 7 ነጥብ 3 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን አምባሳደር ሁ አስታውሰዋል፡፡

ለአብነትም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘው የምስራቅ ኢንዱስትሪ ዞን ከ100 በላይ አምራቾችን አቅፎ ከመያዙም ባሻገር በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ከቻይና-አፍሪክ ቁልፍ የትብብር መስኮች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በፈረንጆቹ መስከረም 8 ቀን 2023 በአዲስ አበባ የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ 10ኛ ዓመት አስመልክቶ የቻይና-አፍሪካ ትብብር እና የአህጉሪቱን ኢንቨስትመንት ማስተዋወቂያ ሴሚናር እንደሚካሔድም ይፋ አድርገዋል፡፡

በመሳፍንት ብርሌ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.