በደሴ ከተማ የሚገኘው የቦሩ ሜዳ ሆስፒታል የኮቪድ19 ቫይረስ ተጠቂዎች የህክምና መስጫ እንዲሆን ተዘጋጀ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 1 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በደሴ ከተማ የሚገኘው የቦሩ ሜዳ ሆስፒታል ለደቡብ ወሎ ዞን እና ለደሴ ከተማ አስተዳደር የኮቪድ19 ቫይረስ ተጠቂዎች የህክምና መስጫ እንዲሆን ተዘጋጀ።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የተደረገውን የህክምና መስጫ ዝግጅት በስፍራው በመገኘት ተመልክተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ሆስፒታሉ ያደረገው ዝግጅት እና የሀኪሞች ተነሳሽነት የሚመሰገን መሆኑን በፌስ ቡክ ገጻቸው አስታውቀዋል።
በሆስፒታሉ ለህክምና ባለሙያዎች ጭምብሎችን ጨምሮ ለአካል ጉዳተኞች የሚሆኑ ሰው ሰራሽ እግሮች፣ ጫማዎች እና ሌሎች ቁሳቁሶች እንደሚመረቱም ገልጸዋል።
በሆስፒታሉ ያለው ዝግጅት እዚህ ደረጃ እንዲደርስ በስራው የተሳተፉ የሆስፒታሉ ሰራተኞች እና የተባበሩ አካላትን አመስግነዋል።
ህብረተሰቡ የቅድመ ጥንቃቄ ተግባራትን በመተግበር ወረርሽኙን ለመከላከል እየተሠራ ያለውን ስራ እንዲያግዝም ጥሪ አቅርበዋል።