በአማራ ክልል አርሶ አደሩ ወደ መኸር እርሻ ሥራ እየተመለሰ ነው – ዕዙ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ከአንዳንድ ኪስ ቦታዎች በስተቀር ሰላማዊ ሁኔታውና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የፈጠረለትን አጋጣሚ በመጠቀም አርሶ አደሩ ወደ መኸር እርሻ ሥራ መመለሱን የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ አስታወቀ፡፡
በተጨማሪም የግብርና ግብአቶች ወደየአካባቢዎቹ እየተጓጓዙ መሆኑን ነው ዕዙ ያረጋገጠው፡፡
ዕዙ ዛሬ ባደረገው ስብሰባ ያለፉትን 20 ቀናት የሥራ እንቅስቃሴ ገምግሟል፡፡
በግምገማውም÷ የተጀመረውን ሰላምና መረጋገት ይበልጥ ለማጽናትና አስተማማኝ ለማድረግ ወታደራዊ ኦፕሬሽኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዕዙ ጥብቅ መመሪያ መስጠቱ ተመላክቷል፡፡
ሙሉ ግምገማው ቀጥሎ ቀርቧል፡፡
ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የተሰጠ ወቅታዊ መረጃ ቁጥር- ሦስት
የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ዛሬ ባደረገዉ ስብሰባ ያለፉትን ሃያ ቀናት የሥራ እንቅስቃሴዎቹን ገምግሟል፡፡
ዛሬ ባደረገዉ ግምገማም በሁለተኛዉ እና በሦስተኛው ዙር ወታደራዊ ኦፕሬሽን በተወሰዱ ርምጃዎች አብዛኞቹ የአማራ ክልል ዞኖች ወደ መደበኛ ሁኔታ መመለሳቸውን አረጋግጧል፡፡
በአማራ ክልል ባሕር ዳርን ጨምሮ የዞንና የወረዳ ከተሞችን በመቆጣጣር፣ እሥረኞችን በማስለቀቅ፣ ለዝርፊያ እንዲመቸዉ ቁልፍ መሠረተ ልማቶችን በማውደምና በአማራ ክልል ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በነፍጥ እና በመንጋ በመናድ እኩይ ፖለቲካዊ ፍላጎቱን ለማሳካት ያለመዉ ጽንፈኛና ዘራፊ ኃይል ፍላጎትና ድርጊት ማክሸፉን ዕዙ በግምገማዉ አረጋግጧል፡፡
የአማራ ክልልንም ከዝርፊያ፣ ወድመትና የመፍረስ አደጋ መታደግ መቻሉን አይቷል፡፡
በመሆኑም የክልሉን ዞኖች ከባሕር ዳር ከተማ ጋር የሚያገናኙትን ጨምሮ ክልሉን ከአዲስ አበባ ጋር የሚያገናኙና ተዘግተዉ የነበሩ ዋና ዋና መንገዶችና መሥመሮች ተከፍተዋል፡፡ አብዛኞቹ መሥመሮች ለትራስፖርትና ለመደበኛ እንቅስቃሴ ክፍት እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡
ሁሉም የመንግሥትና የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተሟላ መደበኛ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡
ሕዝቡ ለመከላከያ ሠራዊት እያሳየ ያለው አቀባበል፣ የስንቅና የማበረታቻ ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መሆኑን ዕዙ በግምገማዉ አረጋግጧል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች በኪስ ቦታዎች እየተሰበሰቡና በቡድን እየተደራጁ መንገድና ሱቆችን ለመዝጋት፣ ዝርፊያና በመሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ለመፈጸም፣ የተዛቡና የተሳሳቱ መረጃዎችን በማሰራጨት ህብረተሰቡን ለመደናገር ቢሞክሩም እንደልተሳካላቸዉ ዕዙ አይቷል፡፡
የተጀመረዉን ሰላምና መረጋገት ይበልጥ ለማጽናትና አስተማማኝ ለማድረግ ወታደራዊ ኦፕሬሽኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዕዙ ጥብቅ መመሪያ ሰጥቷል፡፡
ከዘራፊና ጽንፈኛ ኃይሎች በጸዱ አካባቢዎች የድርጊቱ ዋና ዋና ተዋናዮች በሕግ ቁጥጥር ሥር እንዲዉሉ እየተደረገ መሆኑንም አረጋግጧል፡፡
ከአንዳንድ ኪስ ቦታዎች በቀር ሰላማዊ ሁኔታዉና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የፈጠረለትን አጋጣሚ በመጠቀም አርሶ አደሩ ወደ መኸር አዝመራ ሥራው መመለሱንና የግብርና ግብአቶች ወደየአካባቢዎቹ እየተጓጓዙ መሆኑን ዕዙ አረጋግጧል፡፡
ዕዙ ክልሉ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ እንዲመለስ ላደረጉ የጸጥታ አካላት፣ ለሕዝቡና በየደረጃዉ ላሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የቀጠናና በስራቸዉ ላሉ የኮማንድ ፖስት መምሪያ አባላት በዚህ አጋጣሚ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡ መላዉ የክልሉ ሕዝብ ከጸጥታ ኃይሎች ጎን በመሰለፍ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ያደረገዉን አኩሪ ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ዕዙ ጥሪዉን ያቀርባል፡፡
ነሐሴ 17 ቀን 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ
የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ