የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ስነ- አዕምሮ ህክምና ክፍል ለኮቪድ-19 ህሙማን አገልግሎት መስጠት ሊጀምር ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣2012( ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የስነ-አዕምሮ ህክምና ክፍል ለኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ህሙማን የህክምና አገልግሎት መስጠት ሊጀምር ነው።
በሆስፒታሉ የስነ-አዕምሮ ህክምና ክፍል ሃላፊ ዶክተር አይዳ ከበደ ÷ሆስፒታሉ የኮሮናቫይረስ ላለባቸው ሰዎች የህክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
ቫይረሱ ተገኝቶባቸው ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ አንዳንድ ታካሚዎች አላስፈላጊ ጭንቀት፣ ፍርሃት፣ መረበሽ እንዲሁም የእንቅልፍ ማጣት እንደሚስተዋልባቸው ገልጸዋል።
በዚህም የህክምና አገልግሎቱ የተለያዩ የስነ-ልቦና እና የስነ-አዕምሮ ችግሮች ለታየባቸው ህሙማንም አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።
በኢትዮጵያ ቫይረሱ እንደተከሰተ በየክፍሉ የስነ-ልቦና ህክምና እየተሰጠ የነበረ ቢሆንም ለኮቪድ-19 መከላከያ የሚደረገው ልብስ ከስነ-ልቦና ምክክር ጋር ምቹ ባለመሆኑ በአሁኑ ወቅት ህክምናው በስልክ እየተሰጠ ነው መሆኑን አንስተዋል ።
ይህንንም አገልለግሎት በማሻሻል ሆስፒታሉ ለስነ-አዕምሮና ስነ-ልቦና ህክምና እያስገነባ ያለው ክፍል ተጠናቆ ስራ እንደሚጀምር ነው የገለጹት።
የአዕምሮ ህክምና ክፍሉ የተወሰኑ የማጠናቀቂያ ስራዎች አልቀው በቀጣይ ሳምንት አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም ሃላፊዋ ገልጸዋል።
የኮሮና ወረርሽኝ ከበሽታው በተጨማሪ የስነ-ልቦና መረበሽ ችግር እየሆነ መምጣቱንም ዶክተር አይዳ ጠቁመው÷ለችግሩ መባባስ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች የሚለቀቁ ትክክለኛነታቸው ያልተረጋገጠ መረጃዎችም ምክንያት መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በመሆኑም ከአለም የጤና ድርጅት፣ የጤና ሚኒስቴር እንዲሁም ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ መረጃዎችንና ምክሮችን መከተል ተገቢ እንደሆነ ገልጸው÷ ሳይንሳዊ ምክሮችን በመከተልና ፍርሃትን በማስወገድ በሽታ የመከላከል አቅምን ማጠናከር እንደሚያስፈልግም መክረዋል።
ታማሚዎች አገግመው ከሆስፒታሉ ከወጡ በኋላ በአካል በመምጣት አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉም ነው የተናገሩት።
ሃላፊዋ አያይዘውም በጤና ሚኒስቴር የሚገኝ የስነ-ልቦና እና ስነ-አዕምሮ ህክምና አድቫይሰሪ ካውንስል በተለያዩ ለይቶ ማቆያ ለሚገኙ ሰዎች የስነ-ልቦና ድጋፍና እዳታ እያደረገላቸው ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!