Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የምግብ እጥረት እንዳያጋጥም ተጨማሪ 40 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል ይመረታል- አቶ ዑመር ሁሴን

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ የምግብ እጥረት እንዳይፈጠር ከመኸር ምርት በተጨማሪ 40 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል እንደሚመረት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን ገለጹ።

50 ሚሊዮን ኩንታል አትክልትና ፍራፍሬ ማምረት መጀመሩም ነው የተገለጸው።

አቶ ዑመር ሁሴን  ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የቫይረሱን መከሰት ተከትሎ ምርትና ምርታማነት እንዳይቀንስ ከመደበኛው የእርሻ እንቅስቃሴ በተጨማሪ ምርት የሚጨምሩ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

”የበሽታው ስርጭት በዚሁ ከቀጠለ፣ ምናልባትም ከውጭ የሚገቡት የስንዴ ምርት ቢቆምና አምስት በመቶ ምርት ቢቀንስ የሚል ግምት ወስደን ያንን ሊተካ የሚችል እቅድ አውጥተን እየሰራን ነው” ብለዋል።

በዚህም ዘንድሮ በመኽር ወቅት እርሻ በተጨማሪ 40 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል ለማምረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚያም ባለፈ 50 ሚሊዮን ኩንታል አትክልትና ፍራፍሬ  ለማምረት እንቅስቃሴ መጀመሩን  ጠቁመው÷ለሥራውም ለከተማ ግብርና ትኩረት መሰጠቱን ያመለከቱት አመልክተዋል።

ለዚህም በአዲስ አበባ ከተማ የእንሰሳት ሃብት፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሥራዎች ከማዕከል በተመደቡ ባለሙያዎች  መጀመሩን ገልጸዋል።

የከተማ ግብርና ለኮሮና ቫይረስ ምላሽ ለመስጠት ብቻ ሳይሆን ባለፈው በጀት ዓመት የወጣውን ፖሊሲ በመተግበር እንደሚስፋፋም  ነው የተናገሩት።

ለበልግ ወቅት ምርት ወደ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር የሚሆን መሬት ታርሶ 64 በመቶው ዘር መልበሱን ያስታወሱት ሚኒስትሩ÷ለመኸር ወቅት እርሻ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ከውጭ በመግባት ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

የአገሪቷ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ዘመናዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን አቶ ዑመር መግለጻቸውን  ኢዜአ ዘግቧል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!

https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.