Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፍ የገንዘብ ዝውውር ስርዓትን በመጠቀም ሊፈፀም የነበረ የ110 ሚሊየን ዶላር የገንዘብ ማጭበርበር እና ዘረፋ ወንጀል ከሸፈ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ማጭበርበር እና ዘረፋ ወንጀል ማክሸፉን ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ዝውውር ስርዓትን በመጠቀም 110 ሚልዮን ዶላር የማጭበርበርና የዘረፋ የወንጀል ሙከራ በቁጥጥር ስር እንዲውል ማድረጉን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በመግለጫው ተጠርጣሪዎቹ ነዋሪነቱ አሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት በሆነው ኒል ቻርለስ የተባለ ግለስብ ስም በባንክ የተቀመጠ 110 ሚሊየን ዶላርን የባንክ ሂሳብ ባለቤቱ እንዳዘዘ አስመስለው አዲስ አበባ ከተማ ፊንፊኔ ቅርንጫፍ ተብሎ ከሚታወቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለማውጣት የተለያዩ የማጭበርበር ስልቶችን ሲያቀናጁ እንደነበር አስታውቋል፡፡

ይሁንና ህገወጥ የገንዘብ ማዘዋወርና ዘረፋ ወንጀሉ በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ክትትል ስር የነበረ በመሆኑ፤ግንቦት 1 ቀን 2012 ዓ.ም በመጀመሪያ ዙር 60 ሚሊየን 990 ሺህ 939 ብር ከተጠቀሰው ባንክ አውጥተው በማዳበሪያ ጭነው በአዘጋጁት ተሸከርካሪ ሊወስዱ ሲሉ እዚያው ባንክ ውስጥ እያሉ በፖሊስ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል፡፡

ወንጀሉን በማቀነባበር ከሚታወቁት መካከል አድይሚ አድርሚ አብዱልራፊ (Adeymi Aderemi Abdulrafiu) የተባለ ናይጄሪያዊ ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ሸገር እንግዳ ማረፊያ በቀን 450 ብር እየከፈለ ከአንድ አመት በላይ በመቀመጥ ተልእኮውን ለማስፈጽም ሲንቀሳቀስ እንደነበር ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሲያካሂድ በነበረው ክትትል አረጋግጧል፡፡

ይኸው ግለሰብ ተልእኮውን ለማስፈጸም ዓለም አቀፍ ኤቲም ካርድ ያዘጋጀ ሲሆን፤ገንዘቡንም ከአሜሪካዊው ኒል ቻርለስ የባንክ ሂሳብ ቁጥር በቀላሉ እንደ ባለቤት ሆኖ ለማውጣት ያመቸው ዘንድ በኢትዮጵያ በዘርፉ ልምድ ያላቸውን የሳይበርና የአይቲ ባለሙያዎችን፣እንዲሁም ተያያዥ ሙያ ያላቸውን ግለሰቦች በመለየትና በማጥናት የጥቅም ተጋሪ በማድረግ ሲንቀሳቀስ መቆየቱ ታውቋል፡፡

በዚህ ወንጀል ለጊዜው አንድ ናይጄሪያዊና አምስት ኢትዮጵውያን በድምሩ ስድስት ግለሰቦች በተካሄደው የመረጃ ማሰባሰብና ክትትል በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ቀሪዎችም እንዲያዙ ለማድረግ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ክትትሉን አጠናክሮ መቀጠሉን ነው ያስታወቀው።

ይህንን ዓለም አቀፍ ገንዘብ የማስተላለፍና የመዝረፍ ወንጀል ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በቴክኖሎጂና በሰው ሃይል መረጃ ተደግፎ በጥብቅ ሙያዊ ዲሲፒሊን ከጅምሩ እስከ መጨረሻው ድረስ እየተከታተለና ተገቢውን አመራር እየሰጠ ውጤታማ እንዲሆን ማድረጉንም ጨምሮ ገልጿል፡፡

ብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት በአገር ደህንነትና በህዝብ ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ በአገር ውስጥ የሚፈጸሙ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ወንጀሎችንና ህገወጥ ድርጊቶችን በማክሸፍ የህዝብንና የአገርን ደህንነት እያስጠበቀ እንደሆነ በተከታታይ ካካሄዳቸው ኦፕሬሽኖች በመነሳት ለህዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

የዚህ አይነት ተመሳሳይ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ ህብረተሰቡ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፤ ይህ ኦፕሬሽን የተሳካ እንዲሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አመራሮችና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ላደረጉት ትብብር አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ላቅ ያለ ምስጋና አቅርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.