በኦሮሚያ ክልል የኮሮና ቫይረስን የመከላከል ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ)በኦሮሚያ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተሰራው ስራ የሚገመግም መድረክ እየተካሄደ ነው።
ግምገማው የክልሉ ርእሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ነው እየተካሄደ ያለው።
በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የመከላከል ስራው በክልሉ እንዲጠናከር ተጠይቋል።
በመድረኩ ንክኪ ያላቸውን ሰዎች የመለየት ስራው በሰፊው የተሰራ ቢሆንም ከድንበር ተደብቀው ገብተው ራሳቸውን ለይተው የማያቆዩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ስጋት መሆኑ ተገልጿል።
በተለይ ከኬንያና ሶማሊያ በድንበር አቋርጠው ከገቡ በኋላ ህዝብ ጋር የሚቀላቀሉ ቁጥራቸው ከፍ ብሏል ተብሏል።
የመመርመሪያ ላብራቲቶሪና የለይቶ ማቆያ ስፍራ ዝግጅት በጥሩ ደረጃ ላይ ያለ ቢሆንም የህክምና ባለሙያዎች ራስን መጠበቂያ ቁሳቁስ እጥረት እንዳይኖር መሰራት እንዳለበት ተጠቁሟል።
ምርትን መደበቅ ፣አላግባብ ዋጋ መጨመር በሰፊው የተስተዋለ ችግር መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን በትራንስፓርት በኩል በተለይ የሌሊት ጉዞን ለማስቀረት ሰፊ ስራ መሰራቱ ተነግሯል።
እንዲሁም ቫይረሱን ለመከላከል በመንግሥት እና ሌሎች ተቋማት ሲወሰዱ የነበሩት ጥንቃቄዎች ላይ መቀዛቀዝ እየተስተዋለ መሆኑ ተነስቷል።
በተለይ ማህበረሰቡ እንዳይሰባሰብባቸው የተከለከሉ የሰርግ ፣ ሀዘን እና እድር በመሳሰሉት ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች አሁንም መስተዋሉን የግብረ ሀይሉ ሪፖርት ጠቅሷል ።
የበጎ አድራጎት ስራዎች ለመከላከል ስራው አጋዥ ሆነው እንደቀጠሉና በርካታ ባለሃብቶች ድጋፍ አደርገዋል ተብሏል።
ከዚህ በሻገር የገበያ ስፍራዎችን መጨመር እና ማስፋፋት እንዲሁም በመረዳዳት ረገድ ውጤታማ ስራዎች ተሠርቷል ነው የተባለው ።
በውይይቱ ላይ የኮሮና ቫይረስ በክልሉ እስከ ሰኔ ድረስ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ኪሳራ ሊያስከትል ይችላል ነው የተባለው።
በሀብታሙ ተ/ስላሴ እና አፈወርቅ አለሙ
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።