ኢትዮጵያ የታላቁን ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በመጭው ሐምሌ ወር የመጀመር እቅዷን ተግባራዊ እንደምታደርግ ገለፀች
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 3 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የታላቁን ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በመጭው ሐምሌ ወር የመጀመር እቅዷን ተግባራዊ እንደምታደርግ ገለፀች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመሩትና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የተሳተፉበት መድረክ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የህዳሴ ግድብ የቴክኒክ ኮሚቴ በውሃ መስኖ ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ አማካኝነት የግድቡን ዝርዝር የስራ ሂደት የተመለከተ ሪፖርት አቅርቦ ውይይት እየተከሄደበት ነው።
በሪፖርቱ እንደተገለፀው የሲቪል ምህንድስና ስራው 87 በመቶ ጥቅል የግንባታ ሂደቱ ደግሞ 73 በመቶ ደርሷል።
በመሆኑም በሐምሌ ወር የመጀመሪያውን የውሃ ሙሌት ስራ ለማስጀመር የሚቻልበት የግንባታ ደረጃ ላይ በመደረሱ ይህም ተግባራዊ እንደሚደረግ ዶክተር አንጂነር ስለሺ መናገራቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።
የውሃ ሙሌቱ እንዳይጀመር ግብፅ ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ቅሬታ ማስገባቷን በተመለከተም ኢትዮጵያ ተገቢውን የምላሽ ሰነድ ማዘጋጀቷንም አስታውቀዋል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።