ዜጎች የዲጂታል ክሕሎታቸውን ለሰላም ግንባታ ማዋል እንደሚገባቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዜጎች የዲጂታል ክሕሎታቸውን ለሰላም ግንባታ ማዋል እንደሚገባቸው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴዔታ ሁሪያ አሊ ገለጹ፡፡
የቀድሞው ፌስቡክ የአሁኑ ሜታ ኩባንያ ያዘጋጀው የዲጂታል ክሕሎትና የሰላም ግንባታ አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ ውይይት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
የዲጂታል ቴክኖሎጂው የዜጎችን ሕይወት በማቃለል ረገድ ከፍተኛ ሚና ቢኖረውም ግጭትን በመፍጠር በኩል ደግሞ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረ ነው ተብሏል።
ሚኒስትር ዴዔታዋ÷ የዲጂታል ዓለሙ የፈጠረው ማህበራዊ ሚዲያ የመረጃ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ቢሆንም የጥላቻ ንግግርና ሁከትን በማስነሳት በሰላም ግንባታ ላይ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መንግስት የጥላቻ ንግግርን ለማስቀረት ሕግ ማውጣቱን ጠቅሰው÷ በሀሰተኛ መጠቀሚያዎች የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮችን ለማስቀረት የማህበራዊ ሚዲያ ባለቤቶች ግልፅ ፖሊሲ ሊያዘጋጁና ቁጥጥር ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ሀሰተኛና ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን ለመከላከልና የሰላም ግንባታን ለማፋጠን የዲጂታል ክሕሎት ያለው ዜጋ መፍጠር ይገባልም ማለታቸውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡