Fana: At a Speed of Life!

በሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል የኮሮና ቫይረስ ልየታና ምርመራ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ዕቃዎች በሚስተናገድበት የሞጆ ደረቅ ወደብ የኮሮና ቫይረስ ልየታና ምርመራ መጀመሩን በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ።

ድንበር አቋራጭ የከባድ ተሽከርካሪ ሾፌሮች፣ አስመጪና ላኪዎች፣ የዕቃ አስተላላፊ ትራንዚተሮች፣ የድርጅቱ እና የሌሎች ተቋማት ሰራተኞች በብዛት የሚገኙበት በመሆኑ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብሏል፡፡

በተለይም የድንበር አቋራጭ ከባድ የመኪና አሽከርካሪዎች ለወረርሽኙ ካላቸው ተጋላጭነት አንጻር በወደቡ ገቢ ጭነት ሲያራግፉም ሆነ ወጪ ጭነት ሲጭኑ በሚኖረው ሂደት የዘመቻ ስራው በከፍተኛ ጥንቃቄ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

ከአሁን በፊትም በወደቡ የሰው ንክኪ በሚበዛባቸው አካባቢዎችና ገቢ ጭነት ይዘው የሚገቡ ተሽከርካሪዎችን የጸረ ተህዋስያን ኬሚካል ርጭት የማካሄድ፣ ማንኛውም ሰው ወደ ወደቡ ሲገባ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ እና የሙቀት ልኬት ማድረግ አስገዳጅ ሆኖ እየተሰራበት ይገኛል፡፡

በቅርቡም ከኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር በወደቡ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ የተጀመረ ሲሆን የመጀመሪያው ዙር ናሙና ምርመራ ለተለያዩ በወደቡ ውስጥ ለሚሰሩ ሰራተኞች፣ ለሾፌሮችና ሌሎች ደንበኞች ተደርጓል፡፡

በሞጆ የተጀመረው የናሙና ምርመራ ሥራ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደሚሰራ ድርጅቱ ገልጿል።

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.