ስፓርት

በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተሳተፉ የአትሌቲክስ ቡድን አባላት የማበረታቻ ሽልማት እየተሰጠ ነው

By Feven Bishaw

August 31, 2023

 

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተሳተፉ የአትሌቲክስ ቡድን አባላት የማበረታቻ ሽልማት እየሰጠ ነው።

በመርሐ ግብሩ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳን ጨምሮ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ የአትሌቲክስ ልዑካን ቡድን አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በመርሐ ግብሩ በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ላስገኙ 2 አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው የ60 ሺህ ብር የገንዘብ ስጦታ ተበርክቷል።

በተጨማሪም የብር ሜዳሊያ ላስገኙ 4 አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው 40 ሺህ ብር የተበረከተ ሲሆን÷ የነሃስ ሜዳሊያ ላስገኙ3 አትሌቶች ደግሞ ለእያንዳንዳቸው የ30 ሺህ ብር ሽልማት ተሰጥቷል።

በሻምፒዮናው የቡድን ስራ በመስራት ልዩ ተሸላሚ ለሆኑት አትሌት ፀሐይ ገመቹ እና ያለም ዘርፍ የኃላው የ50 ሺህ ብር ሽልማት መሰጠቱም ተመላክቷል፡፡

በተመሳሳይ ዲፕሎማ ላገኙ አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው የ15 ሺህ ብር ስጦታና ለተሳተፉ 16 አትሌቶች ደግሞ ለእያንዳንዳቸው የ7 ሺህ ብር የገንዘብ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።

 

በሀንጋሪ ቡዳፔስት በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ 2 ወርቅ፣ 4 ብር እና 3 ነሃስ በድምሩ 9 ሜዳሊያዎችን መሰብሰቧ ይታወቃል።

በዚህም ከዓለም 6ኛ ከአፍሪካ ደግሞ 2ኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቅ ችላለች።

በወርቅነህ ጋሻሁን