ባለስልጣኑ ባለፉት 9 ወራት የመንገዶች ግንባታ ስራ አፈፃፀም 70 በመቶ ማሳካቱን ገለፀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የ2012 በጀት አመት የ9 ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን በቪዲዮ ኮንፈረንስ ዛሬ ገምግሟል፡፡
ባለፋት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ የመደበኛ ስራዎች አፈጻጸም ፣ የማሻሻያ ስራዎች ክንውን ፣ የለውጥ ስራዎች አተገባበር እና ሌሎች ተያያዥ ስራዎችን እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን እንዲሁም ቀጣይ አቅጣጫን ያመላከተ ሪፖርት ቀርቦ በኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ምክክር ተካሂዶበታል።
በዚህም ባለፉት 9 ወራት በዋና መንገዶች ማጠናከርና ደረጃ ማሻሻል 77 ኪ .ሜ መንገድ እና በአገናኝ መንገዶች ደረጃ ማሻሻልና ግንባታ እንዲሁም በመንገዶች ከባድ ጥገና 1 ሺህ 183ኪ .ሜ ተሰርቷል ነው የተባለው፡፡
በተመሳሳይም በመንገዶች ወቅታዊ ጥገና 377 ኪ.ሜ እና በመደበኛ ጥገና 6 ሺህ 519 ኪ .ሜ ማከናወን የቻለ ሲሆን በድምሩ 8 ሺህ 156 ኪ .ሜ በላይ የፊዚካል የመንገድ ግንባታ ስራዎችን ማከናወኑ ተገልጿል፡፡
በዚህም ባሳለፍነው ዘጠኝ ወራት አጠቃላይ አፈጻጻሙ በዋና ዋና የመንገድ ግንባታ ስራዎች 70 በመቶ ሆነዋል።
በውይይቱም ለመንገድ ፕሮጀክቶች መዘግየት መንስኤዎች ከወሰን ማስከበር እና ከካሳ ክፍያ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እንዲሁም የተቋራጮች አቅም ማነስ ዋነኛዎቹ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ተገኘ በዘርፉ ያሉ መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ በተለይም ከባለድርሻ አካላት ጋር አሁንም በቅርበት በመስራት የዘርፉን አፈጻጻም ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት እንደሚደረግ ተናግረዋል ።
በበጀት አመቱ ዕቅድ ከተያዘላቸው የመንገድ ግንባታ ጨረታዎች መካከል ባለፉት ዘጠኝ ወራት 15 የመንገድ ፕሮጀክቶች የግንባታ ውል ስምምነት መፈረሙ ተጠቁሟል።
ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው የ42 ፕሮጀክቶችን የግዥ ሂደት ለማጠናቀቅ እና 26 ፕሮጀክቶችን ወደ ግዥ ሂደት ለማስገባት ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተነግሯል።