Fana: At a Speed of Life!

በመንግስት ላይ ከ30 ቢሊየን ብር በላይ የታክስ ጉዳት አድርሷል የተባለው ግለሰብ ላይ ተደራራቢ ክስ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)በመንግስት ላይ ከ30 ቢሊየን ብር በላይ የታክስ ጉዳት አድርሷል የተባለው በረከት አለኸኝ ላይ 7 ተደራራቢ ክስ ተመሰረተበት።

ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ወንጀል ተረኛ ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሹ በረከት አለልኝ በአዲስ አበባ ከተማ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 በተለምዶ አትሌቶች ሰፈር ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነዋሪ ነው።

የፍትህ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በዚህ ተከሳሽ ላይ ተደራራቢ ሰባት ክሶችን አቅርቦበታል።

ከእነዚህ ተደራራቢ ክሶች መካከል በአንደኛው ክስ ላይ የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ንዑስ አንቀጽ 1/2/3/ ላይ የተደነገገዉን መተላለፍ የሚል ክስ ይገኛል።

በዚህም ተከሳሹ ሰለሞን ሙሉ ከዉን በሚባል ሀሰተኛ ማንነት እና ሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ ባለዉ፣ አድራሻዉ በማይታወቅ እና በፈጠራ ሰዉ ስም በመጠቀም በዉክልና ስልጣን ቁጥር ቅ4/1805/1/2010 በነሃሴ 9 ቀን 2009 ዓ.ም ዉክልና በመዉሰድ፤ ቤት በመከራየት የንግድ ምዝገባና የንግድ ስራ ፈቃድ ያወጣ መሆኑ በክሱ ተመላክቷል።

ይህ ተከሳሽ በመስከረም 29 ቀን 2010 ዓ.ም በአዋሽ ባንክ የባንክ ሂሳብ በመክፈት እና ፖስ ማሽን በመረከብ እንዲሁም ሲኤልቢ 000751(0) የሆነ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ ከጁፒተር ንግድ ስራዎች ድርጅት መረከቡ በክሱ ተጠቅሷል ።

በዚህ መልኩ በተለያየ ጊዜ ማለትም በመስከረም 24 ቀን 2011 ዓ.ም እና በመስከረም 22 ቀን 2012 ዓ .ም ፍቃድ በማሳደስ የተመዘገበዉ በአስመጪነት ንግድ ስራ ዘርፍ ሆኖ ሳለ ምንም አይነት እቃ ከዉጭ አገር ሳያስገባ እና የአገር ዉስጥ የዕቃ ግዥ ሳይፈጽም ከወሰደው የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ ደረሰኞችን ማተሙ ተጠቅሷል።

በተለይም ለ339 ግብር ከፋዮች 1 ሺህ 663 ደረሰኞችን በማሰራጨት በ15 የገቢዎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የ25 ቢሊየን 989 ሚሊየን 943 ሺህ 223 ብር ከ.83 ሳንቲም የግብአት ታክስ ተመላሽ የተጠየቀበት እና በንግድ ትርፍ ወጪነት የቀረበ በመሆኑ ሌሎች ግብር ከፋዮች ሀሰተኛና አሳሳች ሰነዶችን መጠቀሙም ተመላክቷል በክሱ።

ተከሳሹ በተጨማሪም ያተመውን ደረሰኝ በማሰራጨት የንግድ ትርፍ ፣ እና የተጨማሪ እሴት ታክስ ማለትም በአጠቃላይ 13 ቢሊየን 147 ሚሊየን 368 ሺህ 295 ብር ከ.35 ሳንቲም ጉዳት ያደረሰ መሆኑም በክሱ ተጠቅሷል።

በተለይም በዚህም 31 ደረሰኞች 27 ሚሊየን 362 ሺህ 797 ብር ከ14 ሳንቲም በህገ ወጥ ተግባር የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ ለማስመሰል በ2010 እና በ2011 የግብር ዘመን ወይዘሮ ሰላማዊት ሀ/ማርያም እና አቶ አለባቸዉ ዘዉዱ የተፈቀደላቸዉ ሂሳብ አዋቂዎች የዉጭ ሂሳብ (ኦዲት) እንደሰሩለት በማስመሰል ለአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ለአራዳ ክ/ከ ግብር ከፋይ ቅርጫፍ ሀሰተኛና አሳሳች እንዲሁም የተጭበረበሩ ሰነዶችን ያቀረበ በመሆኑ በፈጸመዉ የሀሰት ወይም አሳሳች መግለጫዎች እና የተጭበረበሩ ሰነዶች ማቅረብ ወንጀል መከሰሱን ዐቃቤ ህግ ጠቅሷል።

በዚህ መልኩ ተከሳሹ ሌሎችም ተደራራቢ ክሶች በዝርዝር ቀርበውበታል።

የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዐቃቤ ህግ ከክስ ቻርጁ ጋር በማስረጃነት የሰነዶችና የሰው ምስክር ዝርዝሮችን አያይዞ አቅርቧል።

ተከሳሹ ከጠበቃው ጋር በተረኛ ችሎት ተገኝቶ የክስ ዝርዝሩ እንዲደርሰው ተደርጓል።

በዋስትና ጥያቄ አቅርቦ ክርክር ለማድረግ ተዘጋጅተው ለመቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው በጠየቁት መሰረት ፍርድ ቤቱ ዋስትና ላይ ክርክር ለማድረግ በሚል ለፊታችን ሰኞ ከሰዓት በኋላ ተቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.