Fana: At a Speed of Life!

ከሳሪስ አቦ -ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ መንገድ ከ2016 አጋማሽ በፊት ይጠናቀቃል- የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሳሪስ አቦ-ቃሊቲ -ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመንገድ ፕሮጀክት ከ2016 አጋማሽ በፊት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ገለጸ።
የመንገድ ፕሮጀክቱ በፈረንጆቹ 2016 አጋማሽ ለተቋራጭ የተሰጠ ቢሆንም መጠናቀቅ በነበረበት ጊዜ ሳይጠናቀቅ መቆየቱ ተጠቁሟል።
ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት የተያዘለት መንገዱ 50 በመቶ በመንግስት 50 በመቶ ደግሞ በቻይና ኤግዚን ባንክ ብድር ሊሰራ የታቀደ እንደነበር ተመላክቷል።
ሆኖም ብድሩ ባለመሳካቱ ሙሉ በሙሉ ወጪው በከተማ አስተዳደሩ እየተሸፈነ ስለመሆኑ ተገልጿል።
ይህም ለመዘግየቱ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን የባለስልጣኑ የምህንድስና ሬጉላቶሪ ኃላፊ ኢንጂነር ታከለ ሉላና ለፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት ተናግረዋል።
10 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው ይህ መንገድ ሶስት ግዙፍ ድልድዮችን የያዘ ሲሆን÷ አሁን ላይ ከ87 በመቶ በላይ ግንባታው እንደተጠናቀቀ እና ከቀጣይ ዓመት አጋማሽ በፊት ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ይሆናል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ርቀቱን በግማሽ ያህል እንደሚቀንስ እና ከከተማ ባለፈ ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ እንደሆነም አንስተዋል።
በማርታ ጌታቸው
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.