Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ሀገራት አግደውት የነበረውን መደበኛ እንቅስቃሴን ቀስ እያሉ መፍቀዳቸውን ተከትሎ በሀገራቱ ብስክሌቶች ተፈላጊ እየሆኑ መጥተዋል

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት3፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በርካታ የአውሮፓ ሀገራት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አግደውት የነበረውን መደበኛ እንቅስቃሴን ቀስ እያሉ መፍቀዳቸውን ተከትሎ በሀገራቱ ብስክሌቶች ተፈላጊ እየሆኑ መጥተዋል።

በብሪታኒያ፣ ፈረንሳይና ኔዘርላንድስ የ10 ሺዎችን ህይወት የቀጠፈው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መቀዛቀዝን አሳይቷል በሚል ዜጎች ወደ መደበኛ ስራቸው መመለስ እንዲችሉ ገደቦችን ማላላት ጀምረዋል።

ሆኖም ሰዎች ወደ መደበኛ ስራዎቻቸው ሲመለሱ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትን ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ነው እያሳሰቡ የሚገኙት።

ፈረንሳይ ዜጎች ብስክሌትን እንዲጠቀሙ የሚያበረታታ የ20 ሚሊየን ዩሮ ፈንድን ይፋ አድርጋለች።

በበርካታ የሰሜን አውሮፓ ሀገራትም ሰዎች ህዝብ ተጠጋግቶ ከሚገኝባቸው የህዝብ ትራንስፖርት መስጫ አካባቢዎች ለመራቅ ሲሉ ብስክሌትን በመምረጥ ላይ ይገኛሉ።

ይህንንም ተከትሎ የአንዳንድ ኩባንያዎች የብስክሌት ሽያጭ በከፍተኛ መጠን መጨመሩ ነው የተነገረው።

ቫንሙፍ የተባለው ዓለም አቀፍ የብስክሌት አምራች ኩባንያ ከፈረንጆቹ መጋቢት እስከ ሚያዚያ ወር ውስጥ ሽያጩ በ48 በመቶ ማደጉን ነው የገለፀው።

የዚሁ ኩባንያ የብሪታኒያ ሽያጭ በተጠቀሱት ወራት ውስጥ በ184 በመቶ ማደጉ ተመልክቷል።

በብሪታኒያ በትናንትናው እለት የሀገሪቱ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሰዎች ወደስራ ለመሄድ ብስክሌት ቢጠቀሙ ወይም በዕግራቸው ቢጓዙ ሲል መምከሩን ተከትሎ የአንዳንዶቹ የብስክሌት ሻጭ ኩባንያዎች ሽያጭ ዛሬ በ26 በመቶ ከፍ ብሎ ታይቷል።

ሚኒስቴሩ በሀገሪቱ ከተሞች አውራ ጎዳናዎች በርካታ ብስክሌቶችን ማስተናገድ እንዲችሉ ተደርገው እንደሚለወጡም ነው ያመለከተው።

 

ምንጭ፦ ሬውተርስ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.