ጉባዔው ከምክር ቤቱ በቀረበለት ሕገ መንግስታዊ ጉዳይ ላይ የሚመለከታቸው አካላት አስተያየት እንዲያቀርቡ ጥሪ አደረገ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 3 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበለት ሕገ መንግስታዊ ጉዳይ ላይ የሚመለከታቸውን ተቋማት እና ባለሙያዎች አስተያየት እንዲያቀርቡ ጥሪ አድርጓል።
ጉባዔው ባለሙያዎች/ተቋማት የሚሰሙበትን መድረክ ማዘጋጀቱንም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
ወይዘሮ መዓዛ እርምጃው የሂደቱን እና የውጤቱን ተዓማኒነት እንደሚያሳድግም ጠቅሰዋል።
ከዚህ ባለፈም የሕገ መንግስታዊ ስርዓት ባህል በኢትዮጵያ እንዲዳብር ይረዳል የሚል ዕምነት መኖሩንም ጠቁመዋል።
ከሙያ አስተያየት ተቀባይነት ጋር በተያያዘ የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በቀረበው የሕገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ ምላሽ ላይ ለሚሰጠው ውሳኔ ወይም የውሳኔ ሃሳብ ባለሙያዎች የሚያቀርቡትን የሙያ አስተያየት የመመልከት፣ በግብዓትነት የመጠቀም ወይም በማጣቀሻነት ለመውሰድ አይገደድም።
ከዚህ ባለፈም ጉባኤው የሙያ አስተያየት የሚያቀርቡ ባለሙያዎችን ለመስማት ወይም በማናቸውም መንገድ ማወያየት ከፈለገ ሊጋብዛቸው እንደሚችል የተጠቀሰ ሲሆን፥ ይህን የማድረግ ግዴታ እንደሌለበት ተገልጿል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።