የጀርመን ሁለት ከተሞች ከኢትዮጵያ ከተሞች ጋር በትብብር ለመስራት ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጀርመን የሚገኙ የስቱትጋርት እና ሽዋንቤሽ ዠመንድ ከተሞች በከተማ ልማት ላይ ከኢትዮጵያ ከተሞች ጋር በትብብር ለመስራት ተስማሙ፡፡
በከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በጀርመን በሚገኙ የስቱትጋርት እና ሽዋንቤሽ ዠመንድ ከተሞች ጉብኝት እና የልምድ ልውውት አድርጓል፡፡
ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ከሁለቱ ከተሞች ከንቲባዎች ጋር ከኢትዮጵያ ከተሞች ጋር በሚኖረው የሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ መምከራቸውን በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡
የስቱትጋርት እና ሽዋንቤሽ ዠመንድ ከተሞች የኢትዮጵያን ከተሞች በትምህርትና ሥልጠና፣ ከተማን በማዘመን፣ በከተማ ልማት እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ የልዑካን ቡድኑ አባል የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ከጀርመን ፌዴራል ገንዘብ ሚኒስትር ጁዲዝ ሄርመስ እና ከጀርመን የኢኮኖሚ ልማትና ትብብር ሚኒስቴር ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም÷ ሚኒስትር ዴኤታዋ በወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታና በሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች የተከናወኑ የማሻሻያ ስራዎችን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ ት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ከጀርመን ንግድና ኢንዱስትሪ ቻምበር የአፍሪካ ዳይሬክተር ሄይኮ ሻውድርስኪ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸው ንግድን ለማስፋፋት፣ በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን የጋራ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት መክረዋል፡፡