Fana: At a Speed of Life!

መርማሪ ቦርዱ በባህርዳር ከተማ አስተዳደር ማረሚያ ቤት መምሪያ የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን ጎበኘ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ አባላት በባህርዳር ከተማ አስተዳደር ማረሚያ ቤት መምሪያ የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን ጎበኘ።

ቦርዱ ከተጠርጣሪዎች ጋር ውይይት ማድረግን ጨምሮ የተጠርጣሪዎችን የማረፊያ ሁኔታ ጎብኝቷል።

በጉብኝቱም በተጠርጣሪዎች አያያዝ ዙሪያ የተመለከታቸው መልካም ነገሮች እንዲጠናከሩ እና የሚታዩ ጉድለቶች እንዲታረሙ አሳስቧል።

የቦርዱ ሰብሳቢ አዝመራው አንዴሞ በጉብኝቱ ከተጠርጣሪዎች ጋር ስላለው ሰብአዊ መብት አያያዝ ውይይት በማድረግ መረጃ መሰብሰባቸውን ገልጸዋል።

ተጠርጣሪዎች ወደ ማረሚያ ቤቱ ከመተላለፋቸው በፊት ስለነበራቸው ቆይታ በውይይቱ ወቅት ማንሳታቸውን ጠቁመው፤ መስተካከል ያለባቸውን ጉዳዮች እንዳነሱላቸውም ጠቅሰዋል።

በጉብኝታቸው ተጠርጣሪዎች አስፈላጊው ግብዓት በተሟላለት የማረሚያ ቤት ውስጥ ሆነው መመልከታቸውንም ተናግረዋል።

መኝታ፣ መታጠቢያ፣ ባኞ ቤት እና አስፈላጊ የሚባሉ ግብዓቶች በማረሚያ ቤቱ መኖራቸውንም ገልጸዋል።

ከተጠርጣሪዎች ጋር በተደረገ ውይይት እንዲሟሉ የጠየቋቸውን ጉዳዮች እንዲሟሉ ከሚመለከተው አካል ጋር እንደሚመክሩ ጠቁመዋል።

ተጠርጣሪዎቹ የህክምና አገልግሎት ሲያገኙ እንደነበር ማንሳታቸውን የጠቀሱት ሰብሳቢው፤ ተጨማሪ ህክምና ለሚያስፈልጋቸው ደግሞ ማረሚያ ቤቱ አስፈላጊውን እንዲያደረግ ምክረ ሃሳብ ማቅረባቸውንም ገልጸዋል።

ከተጠርጣሪዎች ጋር በተደረገ ውይይትም መልካም የሚባል ግብዓት መገኘቱን ጠቁመዋል።

ከመርማሪ ቦርድ አባላቱ ጋር የተወያዩት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ እና የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ ሌተናል ጀነራል ብርሃኑ በቀለ፤ ተጠርጣሪዎች ወደ ማረሚያ ቤት ከመላካቸው በፊት ከሰራዊቱ ጋር እንዲቆዩና ህክምና የሚያስፈልጋቸውም እንዲታከሙ መደረጉን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ተጨማሪ አልባሳት መሟላትን ጨምሮ ሌሎች ግብዓት እንዲሟሉም ያሳሰበው መርማሪ ቦርዱ፤ በባህርዳር ከተማ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ሰብዓዊ መብት አያያዝ መልካም የሚባል ስለመሆኑም አስታውቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.