የሰውነት ክብደትን ለመቀነስ መወሰድ ያለባቸው መፍትሄዎች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከመጠን በላይ የሰውነት ክብደት መጨመር የተለያዩ የጎንዮሽ ችግሮችን እንደሚያስከትል የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ከመጠን በላይ ውፍረት በተለያዩ ምክንያቶች ሲመጣ እንደየምክንያቶቹ ሁሉ መፍትሄዎቹም የተለያዩ ሲሆኑ፥ በተፈጥሯዊ መንገድ የተመጠነ የሰውነት ክብደት እንዲኖር የሚያስችሉ መንገዶችን መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ ይነገራል፡፡
በተፈጥሯዊ መንገድ የሰውነት ክብደትን ለማስተካከል ምን ዓይነት መንገዶችን እንጠቀም?
1. የፕሮቲን ‘’ዳይት’’ ወይንም ከበፊቱ ባነሰ ለመመገብ የሚያስችል የምግብ ይዘት በማካተት ተፈጥሯዊ የአመጋገብ ስርዓትን በመከተል ሥብን በማቃጠልና በአግባቡ የምግብ መፈጨት እንዲኖር ማድረግ ክብደት ለመቀነስ ያስችላል፡፡
በዚህ ጊዜም በቀን ከሚመገቡት በፕሮቲን የበለጸጉ ምግቦችን ማካተት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም በፕሮቲን የበለጸጉ ምግቦችን መመገብ በቂ ምግብ የተመገብን ያክል እንዲሰማን እና ብዙ የመመገብ ፍላጎትን ይቀንሳል፡፡
2. የተቀነባበሩ ምግቦችን ባለመመገብ የሰውነት ክብደትን መቀነስ ብሎም ጤናማ ማድረግ ይቻላል፡፡ የተቀነባበሩ ወይንም የታሸጉ ምግቦች ብዙውን ጊዜ ከፍተኛ የስኳር፣ የቅባት እና የካሎሪ ይዘታቸው ከፍተኛ ነው፡፡
የታሸጉ ምግቦች ብዙ እንዲመገቡ የመገፋፋት ባህሪ ስላላቸው የሰውነት ክብደት በመጨመር ተወዳዳሪ የላቸውም፡፡
3. የስኳር መጠናቸው ከፍተኛ የሆኑ ምግቦችን ማራቅ ያስፈልጋል፡፡ በአመጋገብዎ ላይ የስኳር መጠንን ጨመሩ ማለት የልብ ችግር፣ የዓይነት ሁለት የስኳር በሽታ እና ካንሰርን ጋበዙ ማለት ነው ሲል ኽልዝላይን ያስጠነቅቃል፡፡
4. ውሃ መጠጣት የሰውነት ክብደትን ይቀንሳል፡፡ በተለይም ከምግብ በፊት ውሃ መጠጣት የረሃብ ስሜት እንዳይኖርና የመመገብ ፍላጎትን በመቀነስ ይታወቃል፡፡
5. በፀረ-ሙቀት አማቂዎች የበለፀገ ተፈጥሯዊ መጠጥ የሆነውን አረንጓዴ ሻይ መጠጣት ስብ በማቃጠል የሰውነት ክብደትን ለመቀነስ ያስችላል።
6. ፍራፍሬና አትክልቶችን ገንቢና ክብደትን የሚቀንሱ ምግቦች ሲሆኑ፥ በውሃ፣ በንጥረ-ምግቦች እና በፋይበር ይዘታቸው ከፍተኛ ከመሆናቸው በተጨማሪ አብዛኛውን ጊዜ የካሎሪ መጠናቸው በጣም ዝቅተኛ ነው።
7. በቂ እንቅልፍ መተኛት ለክብደት መቀነስ በጣም አስፈላጊ እና ውጤታማ ነው፡፡ እንቅልፍ ማጣት የዕለት ተዕለት የምግብ ፍላጎት ሆርሞኖችን መለዋወጥ ስለሚያስተጓጉል የምግብ ፍላጎት አለመቆጣጠርን ያስከትላል።
8. እንቅስቃሴ ማድረግ የሰውነት የስብ ክምችትን በማቃጠል ክብደት በመቀነስ ዓይነተኛ ሚና የሚጫወት ሲሆን፥ ከዚህ በተጨማሪ በሥራ፣ በማህበራዊ ግንኙነት እና በተለያዩ ሁኔታዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ያስችላል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!