በድሬዳዋ ከተማ ለዘመን መለወጫ በዓል በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለዘመን መለወጫ በዓል በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን የከተማ አስተዳደሩ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ።
በዓሉን ምክንያት በማድረግ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ግብረሀይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱም ተመላክቷል።
በቢሮው የንግድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አሚኖ ጣሃ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፣ አስተዳደሩ ምርቶችን በበቂ ሁኔታ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ ከፌዴራል ተቋማትና በአስተዳደሩ ከሚገኙ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበራት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ይገኛል።
ለዚህም በአስተዳደሩ በከተማና በገጠር 13 ወረዳዎች የሚገኙ መሠረታዊ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበራት ዝግጅት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
ማህበራቱ ለበዓሉ የተዘጋጁትን 455 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት እና 933 ኩንታል ስኳር በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እንደሚያከፋፍሉም አመላክተዋል።
በተጨማሪ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ሳምንቱን በሙሉ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በቅዳሜና እሁድ ገበያ በበቂ መጠን ለሸማቹ እንዲቀርቡ መደረጉንና የንግድና ባዛር ኤግዚቢሽን መዘጋጀቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ምርቶችን በመጋዘን አከማችተው እጥረት እንዲፈጠር በሚያደርጉ እና የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ እንዲሁም ከፍጆታ ምርቶች ጋር ባዕድ ነገር ቀላቅለው የህዝብን ጤና የሚጎዱ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም አሳስበዋል፡፡