Fana: At a Speed of Life!

ቢሮ  ገብተው እንዲሰሩ ከተፈቀደላቸው የመንግስት ሰራተኞች ውጭ የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት የሚጠቀሙ ሰራተኞች ከተገኙ መታወቂያቸውን እንደሚነጠቁ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በየተቋማቱ ወደ ቢሮ በመግባት እንዲሰሩ ከተለዩት የመንግስት ሰራተኞች ውጭ  የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት የሚጠቀሙ ሰራተኞች ከተገኙ መታወቂያ የሚነጠቁ መሆኑን የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት  አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መግባቱ ከተረጋገጠበት ቀን ጀምሮ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር በመንግስት የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከ ማሳወጅ ያደረሰው ወረርሽኙ፣ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል ሲባል እጅግ አስፈላጊ ናቸው ከተባሉ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ሰራተኞች በስተቀር በርካቶች በቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ መደረጉም ይታወቃል።

በመሆኑም በየእለቱ ወደ ስራ የሚገቡ የመንግስት ሰራተኞችን የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ሃላፊነቱን በመወጣት ላይ መሆኑን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት ትልቁ  ገልጸዋል።

አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት እየተጠቀሙ ያሉ የመንግስት ሰራተኞች ኢኮኖሚውን ለመደገፍ ብሎም በሽታውን ለመከላከል ቁልፍ ሚና ያላቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን ለማሳለጥና የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሲባል ተቋማት እንደየስራ ባህሪያቸው ሰራተኞቻቸውን በቤታቸው እንዲቆዩ ማድረጋቸው አስፈላጊ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሯ አንስተዋል።

የትራንስፖርት አገልግሎት ከሁሉም ተቋማት የበለጠ ለኮሮናቫይረስ ሊያጋልጥ እንደሚችል የጠቆሙት ወይዘሮ ፍሬህይወት÷ኢኮኖሚው እንዳይጎዳ በተቻለ መጠን ጥንቃቄ እያደረግን አገልግሎት እንሰጣለን ብለዋል።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት የፐብሊክ ሰርቪስ ተጠቃሚዎች የፌደራልና የአዲስ አበባ ተብሎ ተለይቶ ከተሰጠን ቁጥር በላይ ለማስተናገድ ተገደናል ብለዋል።

በመሆኑም ከፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንና ከአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ጋር በመተባበር አስፈላጊ ተብለው ከተለዩ የመንግስት ሰራተኞች ውጭ የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት የሚጠቀሙ ሰራተኞች ከተገኙ የትራንስፖርት መጠቀሚያ መታወቂያቸው ይነጠቃሉ ብለዋል።

የፌደራልና የአዲስ አበባ የመንግስት ሰራተኞች የተለያየ የመውጫና መግቢያ ሰዓት የተደረገው ጥግግቱን ለመቀነስ መሆኑንም ጠቁመዋል ዋና ዳይሬክተሯ።

በመሆኑም የፌደራል ሰራተኞች በአዲስ አበባ እንዲሁም  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኞች በፌደራል የትራንስፖርት ሰዓት መጠቀም እንደማይችሉ ገልጸዋል።

በዚህም ለፌደራል እና ለአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ተግባራዊ ባደረገው የስራ መግቢያና መውጫ ሰአት ማሻሻያ መሰረት የፌዴራል መንግስት ሰራተኞች ማልደው በመነሳት 1፡30 ስራ ቦታቸው የሚደርሱ ይሆናል ተብሏል።

የአዲስ አበባ የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ደግሞ ጠዋት 2፡00 በመነሳት ከረፋዱ 3፡30 ወደ ስራ  እንደሚገቡ ተገልጿል።

የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አሁን ላይ ባሉት 410 አውቶብሶች አገልግሎት በመስጠት ላይ  እንደሚገኝ ኢዜአ ዘግቧል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!

https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.