Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ መንግስት ያስቀመጠውን የክፍያ መመሪያ ለተላለፉ 21 የግል ትምህርት ቤቶች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መንግስት ያስቀመጠውን የክፍያ መመሪያ ለተላለፉ 21 የግል ትምህርት ቤቶች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ስልጠና ጥራት ሙያ ብቃትና ምዘና ማረጋገጫ ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ በሰጡት መግለጫ፥ የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ ከመጋቢት 7 2012 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር አፍ ደረጃ ትምህርት መዘጋቱን አስታውሰው፤ የግል ትምህርት ቤቶች በትምህርት ሚኒስተር ውሳኔ መሰረት ክፍያ እንዲቀበሉ መደረጉን ገልፀዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር የግል ትምህርት ቤቶች ለትምህርት አገልግሎቱ የሚያስከፍሉት ክፍያ ከ50 እስከ 75 በመቶ እንዲሆን በተወሰነው መሰረት አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ይህንኑ ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

ይሁን እንጂ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እውቅና ካገኙ 1 ሺህ 580 ትምህርት ቤቶች መካከል 21 የሚሆኑት ህብረተሰቡን ሙሉ ክፍያ በመጠየቅ ላይ መሆናቸው በመረጋገጡ በአንድ ሳምንት ውስጥ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው አስገንዝበዋል።

እነዚህ21 ትምህርት ቤቶች በተሰጣቸው ማስጠንቀቂያ መሰረት ከመንግስት የወረደውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበው ይህንን በማይተገብሩ ትምህርት ቤቶች ላይ ፍቃድ እስከ መሰረዝ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድም ነው የገለጹት።

ወይዘሮ ሸዊት አክለውም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በስድሰት ክፍለ ከተሞች በሚገኙ 36 ትምህርት ቤቶች ዳሰሳ ከማድረጉ ባሻገር በሁሉም ክፍለ ከተሞች ቁጥጥር የሚያደርግ ቡድን አዋቅሮ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ወላጆች ልጆቻቸው ትምህርት ቤቶቹ ቴሌግራምን ጨምሮ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰጡትን ትምህርትም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አማካይነት በተለያዩ የትምህርት መስጫ መንገዶች የሚተላለፉ ትምህርቶችን በአግባቡ እንዲከታተሉ ማድረግ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.