በአፍሪካ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ከኤች አይ ቪ ጋር ተዛማጅ በሆኑ ምክንያቶች ከ500 ሺህ በላይ ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ – የዓለም የጤና ድርጅት
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአፍሪካ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ከኤች አይ ቪ/ኤድስ በሽታ ጋር ተዛማጅ በሆኑ ምክንያቶች ከግማሽ ሚሊየን በላይ ሰዎች ሊሞቱ እንደሚችሉ የዓለም የጤና ድርጅት አስጠነቀቀ።
የዓለም ጤና ድርጅት ከተመድ ኤድስ ክንፍ ጋር ያደረገው የዳሰሳ ጥናት ትንተና እንደሚያሳየው፥ በወረርሽኙ ምክንያት ለ6 ወራት የፀረ-ኤች አይ ቪ መድሀኒት ቢቋረጥ ከኤድስ ጋር በተዛመዱ በሽታዎች የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እንደሚጨምር ተመላክቷል።
በዚህም ምክንያት በፈረንጆቹ በ2008 በኤድስ ከ950 ሺህ በላይ ሰዎች የሞቱበት ታሪክ ዳግም ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቋል።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሀኖም በሰጡት መግለጫ፥ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች መንግስታት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ካልተንቀሳቀሱ በስተቀር ከግማሽ ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከኤድስ ጋር በተዛመዱ በሽታዎች አሁን እና በሚቀጥለው ዓመት መካከል ሊሞቱ ይችላሉ ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
“በአፍሪካ ከግማሽ ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከኤድስ ጋር ተዛማጅ በሆኑ በሽታዎች ቢሞቱ ክስተቱ አስደንጋጭ ከመሆኑም ባሻገር ወደ ኋላ ታሪክ እንደ መመለስ ያህል ነው” ብለዋል።
ዶክተር ቴድሮስ አያይዘውም ሀገራት ኤች አይ ቪ ያለባቸው ሰዎች ሕክምናቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉና አገልግሎቱ እንዳይቋረጥ ማድረግ ይኖርባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
የተመድ ኤድስ ዋና ዳይሬክተር ዊኒ ቢንያማ በበኩላቸው፦ በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ምክንያት የኤች አይ ቪ ሕክምና እንቅፋት ሊገጥመው ይችላል፤ በዚህም ሕክምና መስጫዎች አገልግሎት ለመስጠት ሊቸገሩ ወይም ሊዘጉ ይችላሉ ሲሉ አስረድተዋል።
አያይዘውም አንዱ በሽታ ለሌላው በሽታ በሚሰጠው ሕክምና ላይ ጥላ ማጥላት የለበትም በማለት ኮሮናቫይረስን ለመዋጋት የሚደረገው ጥረት ኤች አይ ቪን ለማስወገድ የሚደረገው ጥረት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ገልጸዋል።
ይህንን ተጽእኖ ለመከላከል አንዳንድ አገሮች ዜጎች በብዛት መድኃኒትና ሌሎች ተያያዥ ግብዓቶች የሚያገኙበት መንገድ ከማመቻቸት ባለፈ ህመምተኞች ራስን በራስ መመርመሪያ መሣሪያ እንዲያገኙ በማድረግ የሕክምና ባለሙያዎችን ጫና ለማቅለል እየሰሩ መሆኑ ተመላክቷል።
ምንጭ፡-ቢቢሲ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!