በፀጥታ ችግር ፈተና ያልወሰዱ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ከመስከረም 8 ቀን ጀምሮ ይፈተናሉ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፀጥታ ችግርና በሌሎች ምክንያቶች ፈተና ያልወሰዱ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኞችን ለመፈተን መዘጋጀቱን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አስታውቋል፡፡
የ2015 ዓ.ም የኢትዮጵያ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ሰርተፊኬት (12ኛ ክፍል) ፈተና ከሐምሌ 19 እስከ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በሁለት ዙር መሰጠቱን አገልግሎቱ አስታውሷል፡፡
ይሁንና በጎንደርና በጋምቤላ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ሙሉ በሙሉ እና በከፊል 14 ሺህ 891 ተማሪዎች እንዲሁም በሕህ ግ ጥላ ስር በማረሚያ ቤቶች የሚገኙ 419 ተፈታኝ ተማሪዎች ፈተናውን ሳይወስዱ መቅረታቸው ተጠቅሷል፡፡
ተፈታኞችን ከመጪው መስከረም 8 እስከ መስከረም 11 ቀን 2016 ዓ.ም ለመፈተን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ውጤታቸውም ከመጀመሪያው ዙር ጋር እንደሚገለጽም የአገልግሎቱ መረጃ ያመላክታል፡፡