Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያን ከሸማችነት ወደ አምራችነት ለማሸጋገር ሁሉም መረባረብ ይጠበቅበታል – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ተተኪ ምርቶችን በማምረት ኢትዮጵያን ከሸማችነት ወደ አምራችነት ለማሸጋገር ሁሉም ባለድርሻ አካላት መረባረብ እንደሚጠበቅበት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስገነዘበ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጳጉሜን 4 “ከሸማችነት ወደ አምራችነት” በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ የሚገኘውን የአምራችነት ቀንን አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፏል።

በመልዕክቱም ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና ጉልበታቸውንና ሃብታቸውን አፍስሰው ሀገራችንን ከሸማችነት ወደ አምራችነት ለማሸጋገር በሙሉ አቅማቸውና እውቀታቸው እየለፉ ያሉ ትጉህ አምራቾችንና ታማኝ ግብር ከፋዎችን በማመስገን ይሆናል ብሏል፡፡

የመልዕክቱ ሙሉ ቃልም እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ከሸማችነት ወደ አምራችነት

ኢትዮጵያ የትጉህ አምራች ልጆች ሀገር ናት፡፡ ትርፍ አምርተው ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ፣ በአምራች እንዱስትሪ ዘርፍ ተሰማርቶ ምርታቸውን የሚቀርቡ እና ግብርን በታማኝነት በመክፈል ሀገርን ለማሻጋገር ታሪክ እየሰሩ ያሉ ምስጉን አምራቾች መፈጠር ተጀምሯል፡፡

ሀገራችን በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ብታልፍም፤ ብርቱ አምራች አርሶ እና አርብቶ አደሮች ስላሏት የእህል እና የእንስሳት ምርታችን በእጅጉ ከፍ ብሏል፡፡ በተጠኑ የፖሊሲ የለውጥ እርምጃዎች አማካይነት ግብርናችን አስደማሚ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡

በ2015 ዓ.ም በከተማና በገጠር ግብርና በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ዉጤት በውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ በመስኖ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት እና በግብርና ሜካናይዜሽን አቅርቦት ላይ መልካም አፈፃፀም ታይቷል፡፡ ይህ የምርታማነት ስኬት የተመዘገበው በብርቱ አርሶ አደሮቻችን እና በትጉህ የግብርና ዘርፍ አመራሮቻችን የተቀናጀ ርብርብ ነው፡፡

በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በሚሊየን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች የላቀ ምርት አምርተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ስንዴ ይበቅልባቸዋል ተብሎ በማይታሰቡ አካባቢዎች ሳይቀር የቆላ ስንዴ በከፍተኛ ሁኔታ ማምረት ተችሏል፡፡ የበጋ ስንዴ ምርትም አርሷደሮቻችን በክረምት ብቻ ሳይሆን በበጋ ወቅትም ማምረት እንደሚችሉ ግንዛቤ ከመፍጠሩም ባለፈ ዓመቱን ሙሉ ያልተቋረጠ የግብርና ሥራ በሀገራችን ባህል እየሆነ መጥቷል፡፡ ስንዴን በበጋና በክረምት በስፋት ማምረት መቻላችን በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ምርቱን ወደ ውጭ አገር ለመላክ ችለናል፡፡ በዚህ ረገድ የተገኘው ዉጤት ኢትዮጵያን ከስንዴ ሸማችነት ወደ አምራችነት አሸጋግሯታል፡፡

በኢንዱስትሪው ዘርፍም በዘንድሮው ዓመት ፈርጀ ብዙ የምርታማነት ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡ “ኢትዮጵያ ታምርት” በሚል መሪ ቃል በተሰራ ሰፊ የንቅናቄ ሥራ ለዓመታት ተቀናጅቶ ባለመሥራት ተዘግተው የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፋብሪካዎች መልሰው ማምረት ጀምረዋል፡፡ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችን ወደ ሥራ በማስገባት ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውሉ ተተኪ ምርቶች እንዲመረቱ፣ ከዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ እየጨመረና የኢንዱስትሪዎች የመወዳደር አቅም እየጎለበተ እንዲመጣ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

በግብርና ዘርፍ የመጣውን ስኬት በማጠናከር በኢንዱስትሪው ዘርፍም ተተኪ ምርቶችን በማምረት ኢትዮጵያን ከሸማችነት ወደ አምራችነት ለማሸጋገር ሁሉም ባለድርሻ አካላት መረባረብ ይጠበቅበታል፡፡ ዛሬ የአምራችነት ቀንን ስናከብር ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና ጉልበታቸውንና ሃብታቸውን አፍስሰው ሀገራችንን ከሸማችነት ወደ አምራችነት ለማሸጋገር በሙሉ አቅማቸውና እውቀታቸው እየለፉ ያሉ ትጉህ አምራቾችንና ታማኝ ግብር ከፋዎችን በማመስገን ይሆናል፡፡

በአዲሱ የ2016 ዓመትም አምራች ዘርፉ ያሉበትን ተግዳሮቶች በመለየት እና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ሀገርአቀፍ ምርታማነትን ለማሳደግ መንግሥት ከመላው ሕዝባችን ጋር በመናበብ አበክሮ ይሠራል፡፡ ኢትዮጵያ ታመርታለች፤ የህዝቧን ብልፅግናም ዕውን ታደርጋለች፡፡

እንኳን ለጳጉሜን 4/2015 ዓ/ም የአምራችነት ቀን አደረሳችሁ!!

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.