የጀርመን መንግስት ለከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የኮቪድ 19 መከላከል የሚውሉ ድጋፎችን አደረገ
አዲስ አበባ፣ግንቦት 4፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የጀርመን መንግስት ለከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የኮቪድ 19 መከላከል የሚውሉ ድጋፎችን አድርጓል።
ድጋፉን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወ/ማርያም ከጀርመን አምባሳደር ብሪታ ቫግነር ላይ ዛሬ ተረክበዋል።
በስነስርዓቱ ላይ ፕሮፌሰር ሂሩት የጀርመን መንግስት ለረጅም ዓመታት የኢትዮጵያን ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና እና ከፍተኛ ትምህርት ዘርፉን ሲደግፍ መቆየቱን ጠቅሰው÷ በአሁኑ ግዜም ተቋማቱ የኮቪድ 19 ወረርሽን ለመከላከል የሚያደርጉትን ጥረት ለማገዝ የሚያስችሉ ግብዓቶችን በድጋፍ መስጠቱን አንስተዋል።
በዚህ ድጋፍ ኢንፍራሬድ ቴርሞሜትሮችን፣ የእጅ መታጠቢያ ሳሙናዎችን የዋይፋይ ዶንግል እና በእግር ውሃ በማፍሰስ እጅ መታጠብ የሚቻልበት ማሽን መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይሄንንም ለከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት በማከፋፈል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚሰሩትን ስራ እንዲያግዝና በተለይ ሰራተኞች ከቤት ሆነው እንዲሰሩ እንደሚረዳ ጠቁመዋል።
አምባሳደር ብሪታ በበኩላቸው ÷መንግስታቸው ከኢትዮጵያ ጋር ከ50 ዓመታት በላይ የዘለቀ የትብብር ስምምነት እንዳለው እና በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ድጋፍ በማድረግ የ25 ዓመታት የትብብር ድጋፍ ግንኙነት አላቸው ብለዋል።
በአሁኑ ግዜም የጀርመን መንግስት ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ፣ ትምህርት፣ ጤና እና የጨርቃጨርቅ ዘርፍ ሰራተኞችን ለመደገፍ የሚያስችል የ120 ሚሊየን ዩሮ ማዘጋጀቱንም ገልጸዋል።
ፕሮፌሰር ሂሩት ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው በተለይ ቴርሞሜትሮቹ የለይቶ ማቆያና ማገገሚያ ማዕከላት በመሆን ለሚያገለግሉ ዩኒቨርስቲዎች ጠቃሚዎች ናቸው ብለዋል።
ሚኒስትሯ ባስተላለፉት መልዕክትም ተማሪዎች ሳይዘናጉ ከትምህርታው ጋር ተያያዥ የሆኑ ንባቦችን እንዲያደርጉና ራሳቸውን ከቫይረሱ በመከላከል ሌሎች ወገኖቻቸውም እንዲጠነቀቁ እንዲያስተምሩ አደራ ማለታቸውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!