የቤንዚን እና ናፍጣ አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ የምርት ጭማሪ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤንዚን ምርት አቅርቦት ላይ 8 በመቶ እና በናፍጣ ላይ ደግሞ የ5 በመቶ የምርት ጭማሪ መደረጉን የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
በ2015 ዓ.ም 3 ነጥብ 9 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን መሠራጨቱን እና በ2016 ዓ.ም 4 ነጥብ 2 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ እንደሚሠራጭ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ ተናግረዋል፡፡
በ2015 የበጀት ዓመት ለነዳጅ ግዢ ኢትዮጵያ 4 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ማውጣቷን አስገንዝበዋል፡፡
ነዳጅን ለመቆጠብ የሚያስችሉ አሰራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው÷ እስካሁንም በአዲስ አበባ እና ሸገር ከተሞች ላይ የነዳጅ አቅርቦት እና የአስተዳደሩን ሥርዓት የሚያሻሽል አሰራር ከሐምሌ ወር ጀምሮ በአስገዳጅነት እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከመስከረም 2016 ጀምሮም በመላ ሀገሪቱ በሙከራ ደረጃ እንደሚተገበር ነው ያመላከቱት፡፡
ሥርዓቱም እያንዳንዱ የነዳጅ ማደያ ትዕዛዙን እስከ ጅቡቲ ድረስ በኦንላይን ሲስተም የሚያዝበት እንዲሁም ተቆጣጣሪው አካል (ባለሥልጣኑ) ሂደቱን እና ሁኔታውን የሚከታተልበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሥርዓቱ መተግበርም ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች እንዲቀንሱ ማድረጉን ነው ዋና ዳይሬክተሯ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በቀን 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሊትር ቤንዚን ይገባ እንደነበር ጠቁመው÷ ሥርዓቱ ከተዘረጋ በኋላ ግን ፍላጎቱ ወደ 800 ሺህ ዝቅ ማለቱን አንስተዋል፡፡
የኤሌክትሮኒክ የነዳጅ ግብይት ተግባራዊ በመደረጉ አንድ ማደያ ምን ያኅል ነዳጅ ተረከበ፣ ምን ያኅሉን ሸጠ የሚለውን ለመቆጣጠር አስችሏል ብለዋል፡፡
እስካሁንም በቴሌ ብር ከ93 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ የነዳጅ ግብይት መፈጸሙን አንስተዋል፡፡
በመሳፍንት እያዩ
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!