Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ ቅድመ ዝግጅትን በተመለከተ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት የዚህን ዓመት የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ ቅድመ ዝግጅት በተመለከተ ውይይት ተካሄደ።
 
በውይይቱ ላይ የችግኝ ተከላ ቅድመ ዝግጅት በተመለከተ የግብርና ሚኒስቴር ማብራሪያ ያቀረበ ሲሆን የብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴው አባላት፣ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት፣ የክልል ፕሬዚደንቶች፣ ሕዝቡን የማነሳሳት ሥራን የሚከውኑ ተጽዕኖ አሳዳሪ ግለሰቦችን ጨምሮ ዐበይት ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
 
ባለፈው ዓመት የችግኝ ተከላ ወቅት የዜጎች መነሳሳት ፣ ንቁ የመንግሥት አመራር ተሳትፎ ፣ የተቋማት ትብብር እና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እንደነበረ ነው የተገለፀው።

 

እነዚህን መልካም ተሞክሮዎች ማስፋት እንደሚያስፈልግ በውይይቱ ተነሥቷል፡፡
 
የዚህ ዓመት ግብ 5 ቢሊየን ችግኞችን መትከል ሲሆን፣ ለዚህ የሚሆን ብዛት ያለው ችግኘ እንዲፈላ ቅድመ ዝግጅት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ጅማሮዎችን ማስቀጠልን ጠቃሚ መሆኑን በመግለፅ አረንጓዴ ዐሻራ በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት በመላው ኢትዮጵያ 20 ቢሊየን ችግኞችን በመትከል እንደሚቀጥል መናገራቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
 
በተጨማሪም አዲስ አበባን የማስዋብ፣ የከተማ ቱሪዝምን የማስፋፋትና ለመኖር ምቹ የሆነች ከተማን መፍጠር ዓላማው የሆነው ፕሮጀክት ያካተታቸውን የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ገልጸዋል፡፡

ችግኝት መትከልን እንደዘመቻ ስራ ሳይሆን ኑሮ ዘይቤ ማድረግ ይገባል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ለችግኝ ተከላው ከቅድመ ዝግጅት እስከ ተከላ 600 ሚሊየን ብር ወጪ እንደሚደረግ ተገልጿል።

በመጪው የክረምት ወራት 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የችግኝ ተከላ እንደሚካሄድ የሚጠበቅ ሲሆን ለዚህ የሚያስፈልገው 84 በመቶ ችግኝ መፅደቁ ተነግሯል።

በአላዛር ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.