በወላይታ ሶዶ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ላብራቶሪ ስራ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ ክልል ህብረተሰብ ጤና ተቋም ሁለተኛው የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ላብራቶሪ በወላይታ ሶዶ ስራ ጀመረ፡፡
የላብራቶሪ ምርመራ በቅርቡ በሀዋሳ ከተማ አገልግሎት መስጠት የተጀመረ ሲሆን አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግና በማፋጠን በአንድ ጊዜ የ96 ሰዎችን እና በ24 ሰዓታት ውስጥ የ1500 ሰዎችን ናሙና መመርመር የሚያስችል የወላይታ ሶዶ የላቦራቶሪ ምርመራ አገልግሎት በይፋ መጀመሩን የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አቅናው ካውዛ ገልጸዋል፡፡
የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊው እንደገለጹት ቫረሱን በአገር ውስጥ በመመርመር ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ላቦራቶሪ እንዲኖር መንግስት ባደረገው ጥረት ማዕከላትን የማስፋፋት ስራ በመሰራቱ ተናግረዋል።
የሶዶ ላብራቶሪ በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር ቀደም ሲል ናሙና በማሰባሰብ ወደ አዲስ አበባና በኋላም ወደ ሐዋሳ ለመላክ ይወጣ የነበረውን ወጪ የሚያስቀርና ባለሙያውም ለማመላለስ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሳይጉላሉ ስራቸውን በትኩረት ለመስራት እንዲችሉ የሚያግዝ ነው ተብሏል።
ህብረተሰቡንም በአጠረ ጊዜ ቫይረሱ ይኑርበት አይኑርበት በማረጋገጥ ከስጋት የሚገላግል መሆኑ መገለፁን ከደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።